ሪፖርት| ምዓም አናብስት ከሊጉ ወርደዋል

ሪፖርት| ምዓም አናብስት ከሊጉ ወርደዋል

ዛሬ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ወሳኝ ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታ በኢትዮጵያ ቡና 3ለ0 ተሸንፎ ከፕሪሚየር ሊጉ መውረዱን አረጋግጧል።

በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው ወሳኝ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቃዛ ነበር። 27ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ዲቫይን ዋቹኩዋ ከሳጥን አጠገብ ያደረገው ሙከራም የጨዋታው የተሻለ የመጀመሪያ ትዕይንት ነበር።

ቡናማዎቹ ተጭነው መጫወታቸውን በመቀጠል 33ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። የመቐለው ተመስገን ተስፋየ የቡናው ቢኒያም ጌታቸው ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ናይጄሪያዊው አማካይ ዲቫይን ዋቹኩዋ በግሩም ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎታል።

ከዕረፍት መልስ ቡናማዎቹ አጥቅተው መጫወታቸውን በመቀጠል 50ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ዲቫይን ዋቹኩዋ በጥሩ ሩጫ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ቢኒያም ጌታቸው በቄንጥ ማስቆጠር ችሏል።

ጨዋታው በተመሳሳይ ፉክክር ቀጥሎ ልማደኛው የቡናው ዘላለም አባተ ከመሃል ሜዳ የመታውን ግሩም ኳስ ግብ ጠባቂው ሶፎንያስ ሰይፉ አስወጥቶበታል።

መቐለዎች ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ተቸግረው አንድም ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳያደርጉ ሲቀሩ በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን ያስቀጠሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ተጨማሪ ግብ አግኝተዋል። 78ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ወርቃማ ዕድል ያባከነው ቢኒያም ጌታቸው 81ኛው ደቂቃ ላይ ከበፍቃዱ ዓለማየሁ የተሻገረለትን ኳስ መረብ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና 3ለ0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ከ37 ጨዋታዎች 37 ነጥቦችን ብቻ የሰበሰበው መቐለ 70 እንደርታ አንድ ጨዋታ እየቀረ ከሊጉ መውረዱን አረጋግጧል።