በጣና ሞገዶቹ ቤት ስኬታማ ዓመታት ያሳለፈው ሴኔጋላዊ ግብ ጠባቂ ማረፍያው በቅርቡ ይታወቃል።

በሀገሩ ክለቦች ኒያሪ ፣ ጃራፍ እና ጄነሬሽን ፉት እንዲሁም በዴንማርኩ ጃመር ቡጌት ከተጫወተ በኋላ ላለፉት የውድድር ዓመታት በባህር ዳር ከተማ ስኬታማ ቆይታ ያደረገው ሴኔጋላዊው የግብ ዘብ ፔፔ ሰይዶ የውል ዘመኑ መጠናቀቁን ተከትሎ ቀጣይ ማረፊያው በብዙዎች የሚጠበቅ ሆኗል።
ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘቸው መረጃ ከሆነ ባህር ዳር ከተማን ጨምሮ በአህጉራዊ መድረክ የሚሳተፉት የኢትዮጵያ ዋንጫው አሸናፊ ወልዋሎ እና የፕሪሚየር ሊጉ ቻምፒዮን ሲዳማ ቡና በዋናነት የተጫዋቹ ፈላጊ ሲሆኑ ዛሬ አመሸሻ ላይ የተጫዋቹ ማረፍያ እንደሚታወቅ ህጋዊ ወኪሉ ኤዶምያስ በቀለ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።
የዴኒሹን ክለብ ለቆ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ ወዲህ በኮከብ ግብ ጠባቂዎች ምርጫ ላይ ዕጩ ሆኖ ይቀርብ የነበረው ቁመተ መለሎው ግብ ጠባቂ የ2018 የሲቢኢ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኖ መሸለሙ ይታወቃል።

