ሰመረ ሀፍታይ በወልዋሎ ለመቆየት ተስማማ

ሰመረ ሀፍታይ በወልዋሎ ለመቆየት ተስማማ

ወልዋሎዎች የፊት መስመር ተጫዋቹን ውል ለማራዘም ከስምምነት ደርሰዋል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት መጀመሪያ ከአምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ አሳዳጊ ክለቡ ተመልሶ ዓመቱን ያሳለፈው ሰመረ ሀፍታይ በወልዋሎ ያለውን ውል ለተጨማሪ ዓመት አራዝሞ በክለቡ ለመቀጠል ተስማምቷል። ሰመረ የእግር ኳስ ሕይወቱን በወልዋሎ ጀምሮ በራያ ዓዘቦ፣ መቻል እንዲሁም ለሦስት የውድድር ዓመታት በሀዲያ ሆሳዕና መጫወቱ የሚታወስ ሲሆን ወደ ቀድሞ ክለቡ በተመለሰበት ዓመትም የኢትዮጵያ ዋንጫ ማሳካቱ ይታወሳል።

በዛሬው ዕለት ሴኔጋላዊውን ማማዱ ሴክ ለማስፈረም የተስማሙት በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚመሩት ወልዋሎዎች በክረምቱ የዝውውር መስኮት የነፃነት ገብረመድኅንን ውል ለማራዘም ተስማምተው ኢዮብ ዓለማየሁ ፣ በረከት ሳሙኤል ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና ማማዱ ሴክን ለማስፈረም ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።