👉 “ወደ አውሮፓ የመውጣት እቅዳችንን ገታ አድርገን ሀገር ውስጥ መስራትን እንመርጣለን።”
👉 “ተጫዋቾቹ ቢጠፉ ወይም ቢቀሩ ሕጋዊ ሪፖርት እንደምናደርግ ከወላጆች ጋር በሰነድ ተፈራርመን ነበር የሄድነው።”
👉 “እንዲቆጣጠሩ ኃላፊነት የሰጠኋቸው ሰዎች ራሳቸው መመለስ አለመፈለጋቸው የተፈጠሩ ስህተቶች ናቸው።”
👉 “ይህ ውድድር ፕሮፌሽናል ሳይሆን አማተር ነው፤ ተጫዋቾቹ በራሳቸውና በወላጆቻቸው ወጪ ነው የሄዱት።”
👉 “ኤምባሲው ቪዛ የሰጣቸው በቂ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ህይወት መረጋጋት እንዳላቸው አጣርቶና አምኖበት ነው።”
በስዊድን ሀገር የጎቲያ ካፕ (Gothia Cup) ውድድር ላይ በጠፉት ታዳጊዎች ዙርያ ከቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ታዲዮስ ተክሉ ጋር የተደረገ ቆይታ።

በስዊድን ሀገር በተካሄደው የጎቲያ ካፕ (Gothia Cup) የታዳጊዎች የእግር ኳስ ውድድር ላይ ተሳትፈው ስለቀሩትና ስለጠፉት 20 የኢትዮጵያ ታዳጊ ተጫዋቾች በተመለከተ ሶከር ኢትዮጵያ ከቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ታዲዮስ ተክሉ ጋር ያደረገችውን ቃለ መጠይቅ እንደሚከተለው ቀርቧል።
የውድድሩ ዓላማና ሁኔታ?
“ውድድሩ ፕሮፌሽናል ሳይሆን አማተር ሲሆን ታዳጊዎች አቅማቸውን በዓለም አቀፍ መድረክ የሚያሳዩበትና ልምድ የሚያገኙበት ነው። ተጫዋቾቹም ሆኑ የኮቺንግ ስታፉ በራሳቸው ወጪ የተጓዙ ሲሆን ኤምባሲውም ቢሆን የቤተሰብ መረጋጋትንና የመመለስ ሁኔታቸውን አጣርቶ ነው ቪዛ የሰጣቸው።”
የመጥፋታቸው ሁኔታና የተወሰዱ እርምጃዎች
“የቡድኑ መሪዎችና የተወሰኑ አስተዳዳሪዎች ውድድሩ ሊጠናቀቅ 2 ቀን ሲቀረው (ጁላይ 18) አስቸኳይ ጉዳይ ስለነበራቸው አስቀድመው ተመልሰዋል። የቀሩት 18 ተጫዋቾችና 3 የስራ አካላት ግን ጁላይ 20 መመለስ ሲገባቸው አልተመለሱም። ጉዳዩ እንደታወቀም ወዲያውኑ ለጎቲያ ካፕ አዘጋጆች፣ ለስዊድን ፖሊስ እና ለኤምባሲው ህጋዊ ሪፖርት ተደርጓል።”
የወላጆችና የታዳጊዎቹ ፍላጎት
“በኋላ ላይ በተደረገ ማጣራት እንደተረጋገጠው አብዛኞቹ ታዳጊዎች (ወደ 90% የሚሆኑት) ከቤተሰቦቻቸው ጋር አስቀድመው በመነጋገርና ፍቃድ በማግኘት እዚያው ቀርተዋል ወይም ወደ ሌሎች 3 እና 4 የአውሮፓ ሀገራት ተበታትነዋል። የወደፊት እቅዳቸውን በተመለከተም ቤተሰቦቻቸው እንዳይመለሱ እንደሚፈልጉ ተረድተናል።”
የወደፊት ጥንቃቄና እቅድ
“ወደፊት እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች እንዳይደገሙ ከወላጆችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አስገዳጅ የሆኑ አሰራሮችን መዘርጋት ያስፈልጋል። አስተማማኝ ካልሆነና የትናንትና ትንንሽ ህፃናት (ከ11-12 ዓመት በታች) ካልሆኑ በቀር ወደፊት በቡድን ደረጃ ወደ አውሮፓ የመውጣት እቅዳችንን ገታ አድርገን ሀገር ውስጥ መስራትን እንመርጣለን።”
በመጨረሻም…?
“እንደነዚህ ያሉ ነገሮች ሆን ተብለው የሚከሰቱ አይደሉም ድንገተኛ ነገሮች ናቸው። የእኔ ቀድሞ መመለስ ነገሮችን ለመቆጣጠር አለመቻል እና ይህን ነገር እንዲቆጣጠሩ ኃላፊነት የሰጠኋቸው ሰዎች ራሳቸው መመለስ አለመፈለጋቸው የተፈጠሩ ስህተቶች ናቸው። ከዚህ አንፃር እንድትረዱን እንፈልጋለን።”

