መዳረሻው ባህር ዳር ከተማ መሆኑን ቀደም ሲል የገለጽንላችሁ ባለልምድ አማካዩ ውሃ ሰማያዊ መለያ በመልበስ ፊርማውን አኑሯል።
አንጋፋው እና ባለ ልምዱ አማካይ ሽመልስ በቀለ የባህር ዳር ከተማ አዲስ ፈራሚ መሆኑ በይፋ ተረጋገጠ። ከሀዋሳ ከተማ ጋር የነበረውን የሁለት ዓመት ውል በስምምነት አፍርሶ ከተለያየ በኋላ መዳረሻው የጣና ሞገዶቹ ለመሆን ከጫፍ መድረሱን ሶከር ኢትዮጵያ ቀደም ሲል መዘገቧ ይታወሳል። አሁን ደግሞ ተጫዋቹ የባህር ዳር ከተማን ማሊያ በመልበስ በይፋ ፊርማውን አኑሯል።
የእግር ኳስ ዕድገቱን በኮረም ሜዳ ያደረገው ሽመልስ በሀገር ውስጥ ለሀዋሳ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መቻል የተጫወተ ሲሆን፣ ለብሔራዊ ቡድንም ረጅም አገልግሎት መስጠት ችሏል። ከሀገር ውጭ ደግሞ በሱዳኑ ኤል መሪክ እና በሊቢያው አል ኢትሀድ ከተጫወተ በኋላ፣ በግብፅ ሊግ ለድፍን አስር ዓመታት ቆይታ አድርጓል። በዚያም ለፔትሮጀት (የክለቡ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪና አምበል ሆኖ ያገለገለበት)፣ ኤል ጎውና፣ ምስር አል መቃሳ እና ኤን ፒፒ አይ መጫወት ችሏል። በቅርቡ በሀዋሳ ከተማ ያሳለፈውን የአንድ ዓመት ቆይታ አጠናቆ አሁን አዲስ ምዕራፍ በባህር ዳር ከተማ ጀምሯል።

