ከአራት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ የሚደረግበት የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ምን አዲስ ነገር ያስመለክተን ይሆን?

ባህር ዳር ከተማ ላይ የተገነባው እና ከ2007 ጀምሮ ዓለም አቀፍ እና አሁጉራዊ ጨዋታዎች ማሰተናገድ የጀመረው እንዲሁም በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ በአንድ ጨዋታ በርካታ ተመልካቾች በመከታተል ክብረ ወሰን እንደያዘ የሚነገርለት ብዙ አስደማሚ ድባብ ሲያስመለክተን የቆየው ግዙፉ የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከዓመታት የዕድሳት ማሻሽያ በኋላ ዳግም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንዲያስተናግድ በካፍ ጊዜያዊ ፈቃድ ማግኘቱ ይታወቃል።
በግንቦት ወር 2007 ኢትዮጵያ ከሌሴቶ ያደረጉትን ጨዋታ የዋልያዎቹን ድል በማጀብ ዓለማቀፋዊ ውድድሮችን በማስተናገድ ሀገራዊ ሀላፊነቱን ሀ ብሎ የጀመረው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመጨረሻው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡደን ጨዋታውን ያደረገው ጥቅምት 2 ቀን 2014 ከደቡብ አፍሪካ ጋር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ነበር። በጨዋታውም ደቡብ አፍሪካ 3-1 በማሸነፍ የባህር ዳር ስታዲየም ለመጀመርያ ጊዜ ዋልያዎቹ ሽንፈት ያስተናገዱበት ጨዋታ ሆኖ ተመዝግቧል።

ከዚህ በኋላ ሀገራችን ኢትዮጵያ በሜዳዋ ምንም ዓይነት ጨዋታዎችን ማድረግ ተስኗት ስደተኛ በመሆን ያለፉትን ዓመታት በሀገራችን ማድረግ የሚገባንን 14 ጨዋታ ሌላ ሀገር ላይ አድርገናል። ደቡብ አፍሪካ ኦርላንዶ ስታዲየም ላይ ከጋና ጋር ህዳር 2/2014 ካደረግነው ጨዋታ ጀምሮ ታንዛንያ፣ ማላዊ፣ ሞሮኮ፣ ሞዛምቢክ፣ ሊብያ፣ ኮንጎ፣ አይቮሪኮስት በመጨረሻም መስከረም 28/2018 ሩዋንዳ ላይ ከጊኒ ቢሳው ከተጫወትን በኋላ መጋቢት 22/2018 ወደ ሀገራችን በመመለስ ድሬዳዋ ላይ ከሳኦቶሜ ጋር መጫወታችን ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በሜዳዋ መጫወት እንዲኖርባት የተደረገው ጥረት ተሳክቶ በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም የተጀመረው ስኬት ቀጥሎ አሁን ደግሞ ግዙፉ የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ካፍ ባደረገው ተደጋጋሚ ፍተሻ እና ግምገማ እንዲሁም ስታዲየሙን መስፈርቱን እንዲያሟላ በተደረገው ከፍተኛ ጥረት በቅርቡ የባህር ዳር ስታዲየም የብሔራዊ ቡድናችን በመስከረም ወር 2019 በሜዳው ለሚያደርገው ጨዋታ የሚያገለግል ጊዜያዊ የካቴጎሪ 3 (CAT 3) ፈቃድ መስጠቱ ይታወሳል።
ትልቁ ዜና መስከረም 19 ቀን 2019 ኢትዮጵያ ከሴኔጋል ጋር በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ለማስተናገድ ቀጠሮ የተያዘለት የባህር ዳር ስታዲየም ለተመልካች ክፍት ሆኖ እንደሚደረግ የታወቀ ሲሆን ከዚህ ቀደም የነበረውን ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር እና አስደናቂ የደጋፊዎች ድባብ ያስመለክተናል ተብሎ ይጠበቃል።

