ከዋልያዎቹ ጋር ልምምድ ሲሰራ የሰነበተው ተስፈኛው የግብ ዘብ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተቀላቀለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መስከረም አጋማሽ ላይ ከሱዳን እና ከሴኔጋል ጋር ላለበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ዝግጅት ከጀመረ ሁለት ሳምንታት ማስቆጠሩ ይታወቃል። ወደ ዝግጅት ከመግባቱ በፊት ለ40 ተጫዋቾች ጥሪ ቢያደርግም በተለያዩ ምክንያቶች 23 ተጫዋቾች ብቻ በመያዝ ልምምድ በመስራት ላይ የቆየው ብሔራዊ ቡድኑ አሁን ደግሞ ግብ ጠባቂው ብሩክ ዘላለም ስብስቡን ለቆ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑን እንዲቀላቀል ፍቃድ ሰጥቷል።
በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ጥሪ የተደረገላቸው ሰባት ታዳጊዎች ከቀናት በፊት ወጣት ብሔራዊ ቡድኑን ቢቀላቀሉም ተስፈኛው ግብ ጠባቂ ግን እስካሁን ድረስ በዋናው ብሔራዊ ቡድን ልምምድ ሲሰራ የቆየ ሲሆን በዛሬው ዕለት ግን የዋልያዎቹን ስብስብ ለቆ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተቀላቅሏል። ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጫዋቾች ቁጥር 22 የደረሰ ሲሆን በዚሁ ስብስብ ዝግጅቱን የሚቀጥል ይሆናል።

