የነገውን የኢትዮጵያ እና ሱዳን ጨዋታ በምን የቴሌቪዥን አማራጭ መመልከት ይቻላል?

የነገውን የኢትዮጵያ እና ሱዳን ጨዋታ በምን የቴሌቪዥን አማራጭ መመልከት ይቻላል?

በአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ዋልያዎቹ ከሱዳን ጋር የሚያደርጉትን የነገ ምሽት 1 ሰዓት ጨዋታ በብቸኝነት የሚያስተላልፉ ተቋሞች ታውቀዋል።

የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ የሚጀምሩ ሲሆን 48 ሀገራት በኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳ በሚካሄደው የአህጉሪቱ ትልቁ ውድድር ላይ ለሚያሳትፉ 24 ቦታዎች ፉክክራቸውን ይጀምራሉ። ሀገራችን ኢትዮጵያም በነገው ዕለት በገለልተኛ ሜዳ ጁባ ላይ ሱዳንን በመግጠም የማጣሪያ ጉዞዋን የምትጀምር ይሆናል።

ሶከር ኢትዮጵያ ከካፍ ባገኘችው መረጃ መሰረት በቀናት ልዩነት የሚደረጉትን የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎችን የምስል መብት ቢን ስፖርት (beIN Sport) እና ካነል ፕሉስ (CANAL+) ብቻ እንዳገኙ አረጋግጠናል።

የካፍ የረጅም ጊዜ የሚዲያ አጋር የሆነው beIN Sport የማጣሪያ ጨዋታዎቹን በመካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ (MENA) ክልል ፤ ሞሮኮ፣ ግብፅ፣ አልጄሪያ፣ ሊቢያ፣ ጅቡቲ፣ ሞሪታኒያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ቱኒዚያ፣ ቻድ፣ ሞሪሸስ፣ ማዳጋስካር እንዲሁም በፈረንሳይ፣ ስዊዘርላንድ፣ አሜሪካ እና ደቡብ ፓሲፊክ ያስተላልፋል።

ካነል ፕሉስ ደግሞ በፈረንሳይኛ ተናጋሪ ከሰሀራ በታች አፍሪካ ሀገራት ውስጥ ከ30 በላይ በሚሆኑ ሀገራት ጨዋታዎቹን በፈረንሳይኛ ቋንቋ ብቻ በልዩ ሁኔታ ያስተላልፋል ተብሏል።

ይህንን ተከትሎ የነገው የዋልያዎቹ ጨዋታ በቢን ስፖርት እና ካነል ፕሉስ አማራጮች ብቻ ተደራሽ እንደሚሆኑ ካፍ አስታውቋል።