በሀገራችን የሚደረገው ተጠባቂው የዋልያዎቹ ጨዋታ በሀገር ውስጥ የቴሌቪዥን አማራጭ እንደማይተላለፍ ታውቋል

በሀገራችን የሚደረገው ተጠባቂው የዋልያዎቹ ጨዋታ በሀገር ውስጥ የቴሌቪዥን አማራጭ እንደማይተላለፍ ታውቋል

የፊታችን ማክሰኞ ባህር ዳር ላይ የሚደረገው ተጠባቂ የኢትዮጵያ እና ሴኔጋል ጨዋታ በነፃ አየር ሞገድ ለሀገር ውስጥ ተመልካቾች የሚደርስበት ዕድል እንደሌለ ይፋ ሆኗል።

ኬኒያ፣ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳ በ2027 ለሚያስተናግዱት የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ  የማጣሪያ ፍልሚያዎች ዛሬ የሚጀመሩ ሲሆን ዋልያዎቹም በምድብ አስር ከሱዳን፣ ሴኔጋል እና ሞዛምቢክ ጋር ተደልድለው ነገ የማጣሪያ ጨዋታቸውን “ሀ” ብለው ይጀምራሉ።

ድረ ገፃችን ሶከር ኢትዮጵያ ከካፍ ያገኘችውን መረጃ ተመርኩዛ ነገ ጁባ ላይ የሚደረገውን ጨዋታ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት በተመለከተ ቀደም ብላ መረጃ ያጋራቻችሁ ሲሆን በሀገራችን ኢትዮጵያ ባህር ዳር ላይ የሚደረገውን የማክሰኞ ጨዋታ በተመለከተ ደግሞ ተጨማሪ የቀጥታ ስርጭት መረጃ ለማጣራት ሞክራለች።

እጅግ ውብ በሆነው በባህር ዳር ስታዲየም የሚደረገው የማክሰኞ ተጠባቂ ጨዋታ በካፍ ስታንዳርድ መሰረት ቀረፃ እንደሚደረግለት የሰማን ሲሆን በዋናነት በዲኤስ ቲቪ የቀረፃ ልምድ ባካበቱ የፕሮዳክሽን ሰራተኞች ጨዋታው በልዩ ጥራት ተቀርፆ በካፍ ፈቃድ ለተሰጠው ፈረንሳይ ለሚገኘው ካነል ፕሉስ ምስሉ እንደሚላክና ካነል ፕሉስ ጨዋታውን በራሱ አማራጮች ብቻ እንደሚያሰራጭ አውቀናል።

ይህንን ተከትሎ ለሀገር ውስጥ ተመልካቾች አሚኮን ጨምሮ ምናልባት ሌሎች የሀገራችን የቴሌቪዥን ተቋሞ ጨዋታውን ሊያስተላልፉ ይችላሉ የሚሉ መላምቶች የነበሩ ቢሆንም ካፍ በነጻ የአየር ሞገድ (Free-to-Air) የምድብ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ጨዋታዎችን የሚያስተላልፉ ጣቢያዎችን ይፋ ሲያደርግ አንድም የሀገራችን ተቋም እንደሌለ ተስተውሏል።

በዚህም ካፍ በነጻ የአየር ሞገድ ጨዋታዎችን RTI (ኮትዲቯር) ፣ RTNC (ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ)፣ ​CRTV (ካሜሩን)፣ ​Botswana TV (ቦትስዋና)፣ ፣ SABC (ደቡብ አፍሪካ)፣ ​Azam (ታንዛኒያ)፣ ​SNRT (ሞሮኮ)፣ ​OnTime Sport (ግብፅ) እና ​RBS (ሩዋንዳ) እንዲሁም በአውሮፓ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ Ziggo (ኔዘርላንድስ)፣ ፣ Sport TV (ፖርቱጋል)፣ ​Movistar (ስፔን) እና ​DAZN (ጀርመን) የተለየ ነገር በቀጣይ ቀናት እስካልተፈጠሩ ድረስ (ባለቀ ሰዓት ካፍ ያስቀመጠውን ክፍያ የሚፈፅም የሀገር ውስጥ የቴሌቪዥን ተቋም ካልመጣ) ብቻ ጨዋታዎቹን በነፃ ለተመልካቾቻቸው እንደሚያሰራጩ አረጋግጠናል።