ዋልያዎቹ እና የባህር ዳር ስታዲየም…

ዋልያዎቹ እና የባህር ዳር ስታዲየም…

ዋልያዎቹ እጅግ ውብ በሆነ መንገድ ታድሶ ለጨዋታ ዝግጁ በሆነው የባህር ዳር ስታዲየም ያላቸው ቁጥር ምን ይመስላል?

ከ12 ዓመታት በፊት (2007) ላይ ግንባታውን በከፊል አጠናቆ አህጉራዊ እና ሀገራዊ ጨዋታዎችን ማስተናገድ የጀመረው የባህር ዳር ስታዲየም በወቅቱ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ደደቢት እና የሲሼልሱ ኮትዲኦር ባደረጉት ጨዋታ ውድድር የማስተናገድ ኃላፊነቱን “ሀ” ብሎ ጀምሯል። በብሔራዊ ቡድኖች የውድድር መድረክ ደግሞ በወርሀ ሰኔ 2007 ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሌሶቶ ጋር ያደረገችውን ጨዋታ አስተናግዷል። ታዲያ ይህ ግዙፍ ስታዲየም ከአምስት አመታት በፊት የካፍን መስፈርት እንዲያሟላ እግድ ከመጣሉ በፊት አጠቃላይ 11 የዋናው ብሔራዊ ቡድናችንን የነጥብ እንዲሁም የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን አስተናግዷል።

ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በ2007 በሜዳው ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረጉትን የሌሶቶ ጨዋታ 2ለ1 ያሸነፉ ሲሆን በ2010 ከኬንያ ያለ ግብ አቻ ተለያይተው ከዛ በመቀጠል ደግሞ ሁልጊዜም በኩራት የሚነሳውን የኮትዲቫር 2ለ1 ድል ተጎናፅፈው በመቀጠል ማዳጋስካርን 4ለ0 አሸንፈዋል። በቻን የውድድር መድረክ ደግሞ ኢትዮጵያ ኬኒያን በዚሁ ስታዲየም አስተናግዳ 2ለ0 ረታለች።

በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የውድድር መድረክ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ከሌሶቶ ጋር ያለ ግብ አቻ የተለያየችበትን ውድድር ግዙፉ ስታዲየም ሲያስተናግድ ከዛ በመቀጠል በ2014 አዲስ ዓመት ዋዜማ ዚምባብዌን 1ለ0 አሸንፋለች። በመጨረሻም ብሔራዊ ቡድናችን ብቸኛ ሽንፈቱን በሜዳው ባስተናገደበት ጨዋታ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ተደርጓል። በዚህም ደቡብ አፍሪካ 3ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ስንመለከት ዋልያዎቹ በሜዳው ሦስት የወዳጅነት ጨዋታዎችን አከናውነዋል። በዚህም ከሴራሊዮን ጋር የተደረገው ጨዋታ 0ለ0 ሲጠናቀቅ ሀገራችን ኢትዮጵያ ማላዊን 4ለ0 ከዛም ዩጋንዳን 2ለ1 አሸንፋለች።

በአጠቃላይ ብሔራዊ ቡድናችን ገዱ በሆነው የባህር ዳር ስታዲየም ከዚህ ቀደም 8 የነጥብ እና 3 የአቋም መፈተሻ በድምሩ 11 ጨዋታዎችን አከናውኖ 7 ሲያሸንፍ 1 ብቻ ተሸንፎ ቀሪዎቹን 3 ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። ብሔራዊ ቡድናችን በሜዳው በአጠቃላይ 18 ግቦችን ተጋጣሚ ላይ ሲያስቆጥር በተቃራኒው 6 ግብ ተቆጥሮበታል። ነገስ?