ኢትዮጵያዊቷ አጥቂ ዳግም በሀገር ቤት ሊግ እንመለከታታለን

ኢትዮጵያዊቷ አጥቂ ዳግም በሀገር ቤት ሊግ እንመለከታታለን

በታንዛንያው ያንግ አፍሪካ ስኬታማ ቆይታ ያደረገችው አረጋሽ ካልሳ ዳግም ወደ ሀገር ቤት ሊግ ትመለሳለች።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ሴቶች እግርኳስ ውስጥ ከተመለከትናቸው ድንቅ ተጫዋቾች መካከል የምትጠቀሰው አረጋሽ ካልሳ ከጎፋ ዞን ኦይዳ ወረዳ ሸፍቴ ከተማ ከተገኘች በኋላ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሰልጥና በመውጣቷ ይታወቃል። በመቀጠል በመቻል እንዲሁም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በዋንጫ የታጀበ ጊዜን ካሳለፈች በኋላ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ወደ ታንዛኒያ ያንጋ ፕሪንሰስ በማቅናት ስትጫወት መቆየቷ አይዘነጋም።

በያንግ አፍሪካ በነበራት ቆይታ በመጀመርያዎቹ አምስት ወራት ከጨዋታ እርቃ በልምምድ ብቻ መቆየቷ ለእርሷ ፈታኝ የነበረ ቢሆንም ወደ ጨዋታ ከተመለስችበት ጊዜ አንስቶ ብቃቷን በማሳየት ቡድኑ ውጤታማ ማድረግ ችላለች። በ2025 በግሏ የምርጥ ጎል ዘርፍ ተሸላሚ ከመሆኗ በተጨማሪ የታንዛኒያ ሳሚያ ሱፐር ካፕ ዋንጫ አሸናፊ መሆን ችላለች።

ከያንጋ ጋር ያላት የውል ዘመን መጠናቀቁን ተከትሎ በአሁኑ ሰዓት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ዝግጅት እያደረገች ያለችው አረጋሽ ከያንጋ ለተጨማሪ ዓመት ለመቆየት ያደረገችው ድርድር ሳይሳካ በመቅረቱ ዳግም በሀገር ቤት ሊግ ተመልሳ ልትጫወት እንደምትችል እርግጥ ሆኗል።

ይሄን ተከትሎ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሚገኙ ትልልቅ ክለቦች እርሷን ለማስፈረም እያናገሯት እንደሆኑ እና ማረፊያዋ የት እንደሚሆን በቅርቡ እንደሚታወቅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።