👉 “የመጀመሪያ 10 ደቂቃ ላይ የሠራናት ስህተት ዋጋ አስከፍላናለች።”
👉 “አሰልጣኝ እንደመሆኔ መጠን እንኳን 4 ጨዋታ ቀርቶ 30 ሴኮንድ ብቻ ቢቀርም…።”
👉 “እንደ ሀገር የአጥቂዎች ችግር አለብን። ከ30 በላይ ተጫውቶ 13፣14 ጎል ነው ከፍተኛ የተቆጠረው።”
👉 “ከትናንት ወዲያ ይህንን ተናግሬያለሁ…”

በ2027 አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ በሜዳዋ ባሕርዳር ስታዲየም በሴኔጋል 1ለ0 ከተሸነፈች በኋላ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ ምን አሉ?
ስለ ጨዋታው…
“የመጀመሪያ 10 ደቂቃ ላይ የሠራናት ስህተት ዋጋ አስከፍላናለች። በመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ሳይደክማቸው ሊጫኑን ይችላሉ ብለን ተነጋግረን ነበር። ከዛ በኋላ ግን ወደ ጨዋታ ለመመለስ ሞክረን ዕድሎችን ፈጥረናል። ከአጥቂዎቻቸው ተከላካዮቻቸው ደከም ማለታቸውን ስናይ መጫን ጀምረን ነበር። ያገኘናቸውን ዕድሎች አልተጠቀምንም ፤ ያገኘናቸውን ዕድሎች ብንጠቀም ኖሮ ባናሸንፍም አቻ እንወጣ ነበር የሚል ትንቢታዊ ግምት አለኝ።”
ለ90 ደቂቃ አንድም ጊዜ ቆመው ስላልመሩበት ምክንያት
“እኛ የለመድነው አሠራር ነው። በተደጋጋሚ ያገኘናቸው ልጆች ስለሆኑ ልምምዶችን አሠርተን ጨዋታውን ለእነሱ ነው የምንተወው። ታክቲካል እና ግልፅ ስህተቶች ሲኖሩ ብቻ ለማረም እንሞክራለን።”
የአጥቂ መስመር አመራረጥ ላይ ክፍተት አለ?
“እንደ አሰልጣኝ ወቅታዊ ብቃት ያላቸውን ልጆች ትመርጣለህ ፤ ወደኋላ አልመለስም። ጎል የሚደርሱበትን መንገድ እንፈጥራለን ተጫዋቹ ይጨርሳል እንጂ እኛ አንጨርስለትም። ከትናንት ወዲያ ይህንን ተናግሬያለሁ። እያንዳንዱን ተጫዋች ጭንቅላት ማወቅ አትችልም ፤ ሰው ስለቀያየርክ ታስቆጥራለህ ማለት አይደለም። እንደ ሀገር የአጥቂዎች ችግር አለብን። ከ30 በላይ ተጫውቶ 13፣14 ጎል ነው ከፍተኛ የተቆጠረው”
ስለ ጋቶች የዛሬ ክፍተቶች
“ውሳኔው የእኛ የአሰልጣኞች ነው። ጋቶችን በብዙ ነገር ነው ምንጠቀምበት ፤ ዛሬ ደክሞት ነበር? አዎ! ግን በእሱ የምንቀይረው ልጅ በረከት ወልዴ ነበር ተጎዳብን። ከዛ ውጪ ክፍተቶች ነበሩ ግን ልምዱን ለመጠቀም አቆይተነዋል።”
ከምድባችን ምንም ያላሸነፈ ፣ ነጥብ ያላገኘ እና ምንም ያላስቆጠረ ቡድን ስለመሆናችን የተሰማዎት ነገር ካለ?
“ደስ አይለኝም።”
የማለፍ ተስፋ አለን?
“እንኳን 4 ጨዋታ ቀርቶ 30 ሴኮንድ ብቻ ቢቀርም አሰልጣኝ እንደመሆኔ መጠን ወሳኝ ነው።”

