አሠልጣኝ ዩሐንስ ከጣፋጩ ድል በኋላ ምን አሉ?

አሠልጣኝ ዩሐንስ ከጣፋጩ ድል በኋላ ምን አሉ?

👉 “በመልሶ ማጥቃት ነበር ለመጫወት የሞከርነው ፤ ይህ በመጨረሻ በሁለተኛው አጋማሽ ከፍሎናል”

👉 “ከሜዳ ውጪ ማሸነፍ መቻል ለእኛ ትልቅ ድል ነው”

የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ 3ኛ ጨዋታውን ወደ ማፑቶ አምርቶ ከሞዛምቢክ አቻው ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በከነዓን ማርክነህ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል አንድ ለምንም አሸንፏል። ዋልያዎቹ በምድቡ ተስፋቸውን ያለመለሙበት ወሳኝ ድል ካገኙበት ፍልሚያ በኋላ በስታዲየሙ የድህረ ጨዋታ ጋዜጣዊ መግለጫ የተሰጠ ሲሆን የዋልያዎቹ አለቃ አሠልጣኝ ዩሐንስ ሳህሌም ለአጭር ደቂቃ በስፍራው ከተገኙ የመገናኛ ብዙሀን አባላት ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አሠልጣኝ ዩሐንስ ሳህሌ በቅድሚያ ስለ ጨዋታው ሀሳብ ሲሰጡ “ከጨዋታው በፊት እንደተናገርኩት እዚህ የመጣነው ነጥብ ለማግኘት ነው። ምክንያቱም ጨዋታው ለእኛ በጣም አስፈላጊያችን ነው። እዚህ ነጥብ ካላገኘን ምናልባት ከውድድሩም ልንወጣ እንችል ነበር። ስለዚህ ያለንን 100% መስጠት እንደሚገባን እናውቅ ነበር። ቡድኔ ከጠንካራ ተጋጣሚ ጋር ነው የተጫወተው። ሞዛምቢክ በመስመርም በመሀልም የሚያጠቃ ነው። ብዙ የግብ እድሎችንም በመጀመሪያው አጋማሽ ፈጥሯል ፤ እኛ ግን ዲሲፕሊንድ ነበርን። በመልሶ ማጥቃት ነበር ለመጫወት የሞከርነው ፤ ይህ በመጨረሻ በሁለተኛው አጋማሽ ከፍሎናል።” ብለዋል።

ከድሉ በኋላ ስላለው ቀጣዩ ጨዋታ ሀሳባቸውን ተጠይቀው የመለሱት አሠልጣኙ “አሁንም መፋለም አለብን። እንዳልኩት በዲፕሊን ነው የተጫወትነው ፤ እንደ ቡድን ነው የተንቀሳቀስነው። ምናልባት የዛሬው ጨዋታ የበለጠ ሊያነሳሳን ይችላል። ከፊታችን ካሉት ቡድኖች ጋር በነጥብ ያቀርበናል። ቀጣዩ ጨዋታ ሌላ ፍልሚያ ነው። እኛ እንደ ቡድን ነው የምንፋለመው። በሜዳችን በደጋፊዎቻችን ፊት ነው የምንጫወተው ፤ ይሄ ደግሞ ለእኛ ተጨማሪ ጥቅም ይዞልን ሊመጣ ይችላል። በአጠቃላይ ከሜዳ ውጪ ማሸነፍ መቻል ለእኛ ትልቅ ድል ነው።” በማለት የድህረ ጨዋታ አስተያየታቸውን አካፍለዋል።