በ12ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወደ ወልድያ ያቀናው የአምናው የፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልድያን 3-0 አሸንፎ ተመልሷል፡፡ ወልድያ የሚገኘው የሶከር ኢትዮጵያ ተባባሪ ፀሃፊመሃመድ አህመድ የሚከተለውን የጨዋታ ሪፖርት ልኮልናል፡፡
መልካ ኮሌ ላይ በተደረገው የ12ኛ ሳምንት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልድያን 3-0 አሸንፏል፡፡ በጨዋታው ወልድያዎች ግብ ጠባቂያቸው ዘውዱ መስፍንን በቅጣት አቅሌስያስ ግርማን በጉዳት ወደ ሜዳ ይዘው ያልገቡ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩልም በተመሰሳሳይ አዳነ ግርማና ደጉ ደበበ በጉዳት ምክንያት ሳያሰልፍ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡
በጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጫና ፈጥረው የተጫወቱ ሲሆን በተደጋጋሚ ወደ ግብ ለመድረስም ሞክረዋል፡፡ በ5ኛው ደቂቃም ግብ አስቆጥረው ረዳት ዳኛው ከጨዋታ ውጪ ነው በሚል ሳያፀድቁት ቀርተዋል፡፡
ከ10ኛው ደቂቃ በኋላ ወልድያዎች ጨዋታውን መቆጣጠር ቢጀምሩም በተጋጋሚ ወደ ግብ መደረስ አልቻሉም፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ ሊባል የሚችል የግብ እድል የፈጠሩትም በሁለት አጋጣሚሚች በ13ኛው እና 40ኛው ደቂቃ ብቻ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት አድርገዋል፡፡ በዚህም በተደጋጋሚ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊሶች የመጀመርያውን ግብ ከመረብ ያሳረፉት የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 2 ደቂቃዎች ሲቀሩ ነው፡፡ ከቅጣት ምት የተሸገረውን ኳስ አሉላ ግርማ በጭንቅላቱ በመግጨት ወደ ግብነት የቀየራት ሲሆን ለግቡ የወልድያው ግብ ጠባቂ አንተነህ አሳዬ ስህተትም ተጠቃሽ ነበር፡፡
በሁለተኛው አገጋማሽ 50ኛው ደቂቃ ላይ አብይ በየነ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች በሰሩት ስህተት ተገኘችውን ኳስ ሳይጠቀምበት ሲቀር ከ2 ደቂቃዎች በኋላ ፈረሰኞቹ በፈጣን መልሶ ማጥቃት በፍፁም ገብረማርያም አማካኝነት ግብ አስቆጥረው መሪነታቸውን ወደ 2-0 አስፍተዋል፡፡
ከግቧ በኋላ በሁለቱም ቡድኖች መካከል እምብዛም የግብ ማግባት ሙከራዎች ያልተተዋሉ ሲሆን በ60ኛው ደቂቃ አሰልጣኝ ሰብስቤ ይባስ ፍሬው ብርሃንን አስወጥተው ታጁዲንን በማስገባት ቡድኑን ለመማጠናከር ቢጥሩም በሜዳ ላይ የረባ ተፅእኖ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በ79ኛው ደቂቃ ላይም ፍፁም ለራሱ ሁለተኛውን ለቡደኑ 3ኛውን ግብ አስቆጥሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 እንዲመራ አስችሏል፡፡
በ80ኛው ደቂቃ ሁለቱም የተጫዋቾች ቅያሪ ሲያደርጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂው ዳዋ ሁቴሳን በፋሲካ አስፋው ወልድያም በተመሳሳይ አብይ በየነን በአንሳር ኢድሪስ ቀይረዋል፡፡
በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች አለማየሁ ሙለታ የቅዱስ ጊዮርጊስን 4ኛ ግብ ለማስቆጠር ቢቃረብም በግብ ጠባቂው ጥረት ግብ ከመሆን ድናለች፡፡ ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 አሸነናፊነት ተጠናቋል፡፡
ድሉን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ 21 ነጥቦችን በመሰብሰብ መሪው ሲዳማ ቡናን በቅርብ ርቀት ሲከተል ወልድያ በበኩሉ በ5 ነጥቦች የደረጃ ሰንጠረዡን የመጨረሻ ደረጃ ይዟል፡፡