በ2015ቱ የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን እየወከለ የሚገኘው ደደቢት በቅድመ ማጣሪያው የሲሼልሱን ኮት ድ ኦር በሆነ ድምር ውጤት በማሸነፍ የመጀመሪያውን ዙር ተቀላቅሏል። ደደቢት ከ2 ሳምንት በፊት በፕራስሊን የተደረገውን ጨዋታ 3-2 ማሸነፍ ችሎ የነበረ ሲሆን ዛሬ በባህርዳር ብሔራዊ ስታዲየም በተደረገው የመልስ ጨዋታ ስዩም ተስፋዬ እና ዳዊት ፍቃዱ ባስቆጠሯቸው ግቦች 2-0 አሸንፏል።
ደደቢቶች በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ተጭነው መጫወት የቻሉ ሲሆን በዳዊት ፍቃዱ አማካኝነት የመጀመሪያውን የግብ ዕድል ለመፍጠር 2 ደቂቃዎች ብቻ ፈጅቶባቸዋል። ተጋጣሚያቸውን በኳስ ቁጥጥር መብለጥ የቻሉት ደደቢቶች በ11ኛው ደቂቃ ስዩም ተስፋዬ ከመአዘን ምት የተሻገረችን ኳስ በመግጨት ግብ አስቆጥሯል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኑሚ ሁለት ጥሩ ዕድሎችን ያገኘ ቢሆንም በግቡ አግዳሚ እና በግብ ጠባቂው ጂን ፖል ሌስፔራንስ ጥረት ግብ ከመሆን ተርፈዋል። በኮት ድ ኦሮች በኩል በግሉ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የቀኝ መስመር ተጫዋች ጄራርድ ባሳት ከደደቢቱ ግብ ጠባቂ ሱሌማና አቡባክሪ ጋር ፊት ለፊት መገናኘት ቢችልም ያገኛቸውን አጋጣሚዎች ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል። ባዶ ጎል የተሳተበት የብርሃኑ ቦጋለ የግንባር ኳስ እና የሳምሶን ጥላሁን በ25ተኛው ደቂቃ በጉዳት በሄኖክ ኢሳያስ ተቀይሮ መውጣት ሌሎቹ የመጀመሪያው ግማሽ አበይት ክስተቶች ነበሩ።
በሁለተኛው ግማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ ጅማሬ እንደመጀመሪያው ያህል የግብ ዕድሎች ባይፈጠሩም ደደቢቶች በሄኖክ ኢሳያስ እና ሳሙኤል ሳኑሚ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በ68ተኛው ደቂቃም ከሄኖክ የተጣለለትን ኳስ ባግባቡ በመጠቀም ዳዊት ፍቃዱ የደደቢትን ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል። በ73ተኛው ደቂቃ የመሃል ተከላካዩ አዳሙ መሃመድ በሰራው ስህተት የኮት ድ ኦሩ አጥቂ ዲን ሱዜቴ የግብ አጋጠሚ ተፈጥሮለት የነበረ ቢሆንም አዳሙ ከኋላ በሰራበት ጥፋት ምክኒያት ለመጠቀም አልቻለም፤ በዚህ ሂደትም አዳሙ መሃመድ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ እንዲወጣ ሆኗል። ከዚህ በኋላ እንግዳው ቡድን ያለውን የቁጥር ብልጫ ለመጠቀም ጥረት ቢያደርግም ይህ ነው የሚባል የግብ አጋጣሚ መፍጠር አልቻለም። በአንፃሩ የደደቢቱ አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ አጥቂውን ሳሙኤል ሳኑሚ በመሃል ተከላካዩ ምኞት ደበበ ቀይረው በማስወጣት የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ጥረት አድርገዋል።
የኮት ድ ኦሩ የመሃል ሜዳ ተጫዋች ጂን ቲጉና የጨዋታው ኮከብ በመባል ከቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው እጅ ሽልማት የተቀበለ ሲሆን የኮት ድ ኦር ባለቤት እና ፕሬዘዳንት ሮበርት ፎዬት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ የማስታወሻ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
ደደቢት በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር የቡርኪናፋሶውን አርሲቢ ክለብ በድምር ውጤት 4-0 ካሸነፈው የናይጄሪያው ዋሪ ዉልቭስ ጋር ይፋለማል።