የጨዋታ ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመከላከያ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲጀምር 9:00 ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመከላከያ ያደረጉት ጨዋታ ያለግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ሁለቱም ቡድኖች በፍጥነት ወደተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ቢታይም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ተስኗቸው ተስተውሏል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ አስደንጋጭ ሙከራ በ10ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳሊሶ ከማራኪ ወርቁ ተቀብሎ ወደግብ የሞከረውን ኳስ የንግድ ባንኩ ግብ ጠባቂ ፌቮ ድንቅ ብቃት ግብ ከመሆን ታድጎታል። መከላከያ በ25ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ የተጫዋች ለውጥ ለማድረግ የተገደዱ ሲሆን ምንይሉ ወንድሙ ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ወጥቶ ካርሎስ ዳምጠው እሱን በመተካት ገብቷል።

በቀሪ የመጀመሪያ ግማሽ ደቂቃዎች ንግድ ባንኮች ከርቀት ግብ ጠባቂውን በመፈተን ግብ ለማስቆጠር የሞከሩ ሲሆን በአንፃሩ የመከላከያ ተጫዋቾች ኳስን ይዘው ወደተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል፡፡ ዳኛቸው በቀለ ፣ ታዲዮስ ወልዴ እና ዮናስ ገረመው ከርቀት ወደግብ ሞክረው በግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ጥረት ግብ ከመሆን የተረፉ ሙከራወች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል የሚጠቀሱ ሙከራዎች ሲሆኑ ቴዎድሮስ በቀለ በጥሩ ሁኔታ ያሻገረውን ኳስ ማራኪ ወርቁ ከቅርብ ርቀት አግኝቶ ቢሞክርም ፌቮ ያወጣበት መከላከያ ያገኘው ወርቃማ አጋጣሚ ነበር።

ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜም በተመሳሳይ እንቅስቃሴ የቀጠለ ሲሆን ታዲዮስ ወልዴ እና ሳሙኤል ዮሐንስ ከርቀት አክርረው በመምታት ለንግድ ባንክ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡

በመከላከያ በኩል ሳሙኤል ታዬ ከማራኪ ወርቁ እና በኋላም ማራኪን ተክቶ ከገባው የተሻ ግዛው ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ባንክ የግብ መስመር መድረስ ቢችሉም የተበላሸ የመጨረሻ የኳስ ንክኪ ስለነበራቸው ግብ ለማስቆጠር አልቻሉም ነበር፡፡

ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ9 ነጥብ በነበረበት 10ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ መከላከያ በ15 ነጥብ ነገ የ9ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎች እስኪደረጉ ድረስ ደረጃውን ወደ 4ኛ ማሻሻል ችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *