የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 14ኛ ሳምንት
መጋቢት 6 ቀን 2007 ዓ.ም ፣ 10፡00
አበበ ቢቂላ ስታድየም
ታክቲካዊ ትንታኔ – በሚልኪያስ አበራ
በዘንድሮው የውድድር ዘመን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን የእርስ በእርስ ፍልሚያ ጨምሮ ለ4ኛ ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች የእሁዱን ብቸኛ የሊግ መርሃ ግብር በአበበ ቢቂላ ስታድየም አካሂደዋል፡፡
የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ቡድን የበላይ በሆነበት የእለቱ ጨዋታ ከሁለቱ የተከላካይ አማካዮች ለአንደኛው (14.ደረጀ መንግስቴ) ነፃ ሚና (free role) የሰጠ 4-2-3-1 የተጨዋቾች የሜዳ ላይ አደራደርን የተገበረ ሲሆን ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 4-3-3 ፎርሜሽንን ተጠቅሟል (ምስል 1)
የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ሂደት
የባለሜዳ ተራነቱን የወሰደው ባን ከዚህ ቀደም አዘውትሮ ከሚጠቀምበት ቀጥተኛ 4-1-4-1 ፎርሜሽን በተለየ በ4-2-3-1 የተደራጀ የመከላከል እና የመልሶ ማጥቃትን የሚተገብር አጨዋወትን ይዞ ገብቷል፡፡ አሰልጣኝ ፀጋዬ በፎርሜሽኑ አተገባበር ለሁለቱ የተከላካይ አማካየጦች የሰጠው ሚና የተለያየ ነበር፡፡ አምበሉ ታድዮስ ቡድኑ በመከላከል ሒደት (defending phase) ሲጫወትም ሆነ በማጥቃት እንቅስቃሴ () ላይ የነበረው ሚና ተመሳሳይ ነበር፡፡ ይህም ለተከላካዮች (Back-4) ሽፋን መስጠት ነበር፡፡ ተጋጣሚ በፈጣን ሽግግር (fast break) ወይም በመልሶ ማጥቃት (counter attacking) አጨዋወት ጥቃት ሊፈፅም ሲዘጋጅ ታድዮስ በተደጋጋሚ ከተከላካይ ክፍሉ ፊት ለፊት የሚገኘውን ቦታ በአግድሞሽ እንቅስቃሴ (lateral movement) ሲያካልል እና ሲሸፍን አምሽቷል፡፡
ሌላኛው የቦታው ተጫዋ ደረጄ መንግስቱ ‹‹ ነፃ ሚና ›› የተሰጠው የንግድ ባንክ የተከላካይ አማካይ ነበር፡፡ ደረጄ በቡድኑ የማጥቃትም ሆነ የመከላከል አጨዋወት ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ነበር፡፡ በተለይ በሜዳው ቁመት ከሳጥን ሳጥን በመመላለስ በሁለቱም የጨዋታ ሒደቶች (attaking and defending phase) ላይ አይነተኛ ሚና ነበረው፡፡
በጨዋታው ንግድ ባንክ ይበልጥ መከላከል ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡ በተጫዋቾች የአግድሞሽ አደራደር (raws) መካከል የነበረው ክፍተት የጠበበ በመሆኑም የቡናዎች ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች (through-balls) በቀላሉ በባንክ ተከላካዮች እና የተከላካይ አማካዮች ቁጥጥር ስር ሲውሉ ተስተውሏል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎች በመሃለኛው ክፍላቸው ላይ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ቢያሳዩም የተጋጣሚያቸውን የተጠቀጠቀ (compact) የመከላከል አጨዋወት ሊሰብር የሚችል አጨዋወት አልተገበሩም፡፡ በተለይ በተከላካይ አማካያቸው (ደረጀ ኃይሉ) ሁለት ጎኖች የነበሩት ዳዊት እና መስኡድም ቦታን ጠብቆ የመጨወት ችግር (positioning) ጎልቶ ታይቷል፡፡
ሁለቱ ቴክኒካዊ ክህሎት ያላቸው አማካዮች አላስፈላጊ የሆነና ቡድኑን የሚያጋልጥ ተደጋጋሚ የቦታ ሽግግር እና ወደ ቀኙ መስመር ያደላ ተደራራቢ እንቅስቃሴ ተጋጣሚያቸው በግራው መስመር የተሸለ ነፃነትን እንዲያገኝ እና የማጥቃት ትኩረት አማራጮጩን በዛው ጎን እንዲያደርግ አግዞታል፡፡
የቡናው የግራ መስመር ተከላካይ አህመዲን እና የቦታው አማካ/አጥቂ (left wide forward) ጥላሁን ቦታውን በመከላከል አጨዋወት በጥሩ ሁኔታ ሲሸፍኑት መዋላቸው እንጂ ቡናዎች ወደ ቀኝ መስመር በማዘንበላቸው በአብዛኛው መስመሩ ክፍት ነበር፡፡
(ምስል 2)
ሁለተኛው 45
ቡናዎች በዚህኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የመጀመርያ ደቂቃዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ነበራቸው፡፡ ነገር ግን በተጋጣሚ ክልል የማጥቃት ወረዳ (attacking third) ላይ የነበራቸው የማጥቃት አቅም እጅጉን ውስን ነበር፡፡ ከተጋጣሚያቸው የተደራጀ የመከላከል ብቃት በተጨማሪ የራሳቸው (የቡናዎች) ታክቲካዊ ስህተቶች ሊጠቀሱ የሚችሉ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረግ ሸግግር ላይ (offensive/attacking transition) በላይኛው የሜዳ ክፍል (higher-up the pith) የሚገኙ ተጫዋቾች ቁጥር አናሳ የሚሆንበት አጋጣሚ በርካታ ነበር፡፡ አስቻለው እና ቢንያም በተደጋጋሚ በመልሶ ማጥቃት እና ፈጣን ሽግግር የሚገኙ ኳሶችን በዚህ ክልል ሊቆጣጠሩ ቢችሉም ኳስን የሚቀበላቸው /ሊያቀብሉት የሚችሉት/ ተጫዋች ሲያጡ እና ኳሱ ሲመክን ታይቷል፡፡ በተለይ ዴቪድ በሻህ (የቀኝ መስመር ተከላካይ) ወደኋላ ባፈገፈገ መከላከል ላይ በማተኮሩ ቡናዎች በመስመር ላይ ለሚኖራቸው ሽግግር (flank transition) አስተዋፅኦው እጅግ አስፈላጊ ቢሆንም ተግባራዊ ሊያደርገው አልቻለም፡፡
ከዚህ ቀደም እንደታየው ዴቪድ በፊት ለፊት እንቅስቃሴ (overlapping movement) ለመሃል አማካዮች እና ለመስመር አጥቂዎች የመቀባበያ አማራጮችን (passing lane options) እንዲሁም የማጥቃት ማእዘናትን (attacking angles) ማስፈት ላይ ችግር ይታይበታል፡፡ ኢትዮ-ጀርመናዊው ጥሩ የመከላከል ችሎታ ስላለው ከ4-3-3 ይልቅ ሌሎች (በተለይም በ4-5-1 ፎርሜሽን) የሚስማሙት ይመስላል፡፡ (ምስል 3)
የንግድ ባንክ የተደራጀ ውጤታማ አጨዋወት
በተደራጀው የመከላከል አጨዋወታቸው (organized defending system) እና በተጫዋቾች የአግድሞሽ አደራደር (raws) መካከል የነበረውን ክፍተት ማጥበብ በመቻላቸው የተጋጣሚያቸውን ቀጥተኛ የማጥቃት አጨዋወት ወደ ሌላ ዘዴ እንዲቀየር አስችለዋል፡፡ ቡናዎች በቀጥተኛ የማጥቃት አጨዋወት (direct play) የንግድ ባንክን የተከላካይ መስመር ማለፍ ሲሳናቸው በሜዳቸው በሜዳው አግድሞሽ የሚላኩ ረጃጅም ቅብብሎች (long diagonal passes) ላይ እንዲያተኩሩ ተገደዋል፡፡ በእርግጥ በዚህ አጨዋወት መጠነኛ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ በ59ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር በኩል ያገኛት የቅጣት ምትም የዚህ አጨዋወታቸው ውጤት ነበረች፡፡ ሆኖም ውጤታማ ሆነው አልዘለቁበትም፡፡
የአሰልጣኝ ፀጋዬ ቡድን ተጋጣሚን በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት በተለይም በቀኝ መስመር በኤፍሬም አሻሞ አማካኝነት ሁለት ወሳኝ የግብ ሙከራዎች አድርጓል፡፡ ቡድኑ የተጋጣሚ የመከላከል ቅርፅ ወደነበረበት ሳይመለስ ጥቃት የሚፈፅምበት መንገድ በማጥቃት አጨዋወቱ ላይ ካሉት ጠንካራ ጎኖቹ አንዱ ነበር፡፡ በ78ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር በመልሶ ማጥቃት ከተከላካዩ የተላከለትን ኳስ ኤፍሬም በጥሩ ሁኔታ ለሰለሞን ሰጥቶት ሰለለሞን ወደ ግብ የላካትን ኳስ በእለቱ ጥሩ የነበረው የቡናው ግብ ጠባቂ ጌቱ ተስፋዬ ቢመልሳትም በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ሲሳይ ቶሊ ግቧን አስቆጥሮ ባንክ ሙሉ 3 ነጥብ እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡
ንግድ ባንኮች ሌላኛው ሳይጠቀስ ማለፍ የሌለበት ጠንካራ ጎናቸው ኳስን ባማከለ እቅስቃሴ (ball oriented movement) ተጋጣሚን በቁጥር በመብለጥ (overload) ኳስን የሚቀሙበት መንገድ ነው፡፡ በዚህ አጨዋወታቸው ላይ የፊት አጥቂው ፊሊፕ ዳውዚን ተሳታፊ የሚያደርግ አጨዋወት ቢጨምሩበት የተሸለ ውጤታማ ቡድን መፍጠር ይችላሉ፡፡ በእለቱ ፊሊፕ ከቡድኑ ተነጥሎ (separated) መዋሉ የቡድኑ ድክመት ነበር፡፡
(ምስል 4)