በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት መከላከያ ዳሽን ቢራን አስተናግዶ 3-1 በሆነ ውጤት አሸንፎ ደረጃውን አሻሽሏል፡፡
ግብ በማግባት ቅድሚያውን የያዙት መከላከያዎች ሲሆኑ በ22ኛው ደቂቃ ተክለወልድ ፍቃዱ በግንባሩ በመግጨት ጦሩን መሪ አድርጓል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኋላ በሁለቱም በኩል በርካታ የግብ ሙከራዎች የተደረጉ ሲሆን ዳሽን በየተሻ ግዛው ፤ መከላከያ ደግሞ በሙሉአለም ፣ መሃመድ እና ሙሉጌታ አማካኝነተ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም ግብ ሳይቆጠር የመጀመርያው አጋማሽ በመከላከያ 1-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡
ዳሽን አቻ የሆነበትን አጋጣሚ ያገኘው ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ነው፡፡ የመከላከያው ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው በግብ ክልሉ የተሸ ግዛውን በመጥለፉ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ በእለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው የተሻ ግዛው የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሮ ዳሽን ቢራን አቻ አድርጓል፡፡
ከግቧ መቆጠር በኋላ የ2ኛውን አጋማሽ በጎዶሎ የተጫወቱት መከላከያዎች ከእንግዶቹ በተሻለ በርካታ ጌዜ ወደ ግብ ቀርበዋል፡፡ አማካዩ ተክለወልድ ፍቃዱ በ77ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት በግሩም ሁኔታ ግብ አስቆጥሮ መከላከያን በድጋሚ መሪ አድርጓል፡፡ ወደኋላ አፈግፍገው በመልሶ ማጥቃት ሲጫወት የነበረው መከላከያ በ82ኛው ደቂቀቃ ሳሙኤል ታዬ ከሚካኤል ደስታ የተሻገረለትን ኳስ ወደግብነት ቀይሮ ጨዋታው በመከላከያ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በጨዋታው መከላከያ ያስቆጠራቸው ሶስቱም ግቦች በሃገራችን ባልተለመደ ሁኔታ በግምባር በመግጨት የተቆጠሩ መሆናቸው በቦታው የተገኙ ተመልካቾችን አስገርሟል፡፡