ባሳለፍነው አመት ከከፍተኛ ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዳግም ያደገው ወልዲያ በመጪው እሁድ በዘመናዊው ሼሄ መሀመድ ሁሴን አላሙዲ ስታድየም የመጀመርያውን ጨዋታ ያደርያል፡፡ ነገር ግን ከዚህ መልካም ዜና ባሻገር ክለቡ በችግሮች እየተፈተነም ይገኛል፡፡
በ10ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወልድያ ትላንት በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ከተረታ በኃላ በክለቡ ያለው ችግር ይፋ መውጣት ጀምሯል፡፡
ለክለቡ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሶከር ኢትዮጲያ እንደገለፁት ከሆነ የቡድኑ አባላት ከበርካታ ችግሮች ጋር እየታገሉ ውድድራቸውን እያካሄዱ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ የቡድኑ አባላት የመጫወቻ ትጥቆች ፣ የትራንስፖርት አቅርቦት ፣ የሆቴል አገልግሎት የመሳሰሉ ለእግርኳስ ክለቡ መሟላት ያለባቸውን መሰረታዊ ነገሮች በአግባቡ እየተሟሉላቸው እንዳልሆነና ይህም በክለቡ ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እያሳደረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ምንጮቻችን አያይዘው እንደገለፁት ከሆነ ችግሩ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ቡድኑ በ2007 የውድድር ዘመን እንዳጋጠመው ወደ ሊጉ በመጣበት አመት ዳግም ወደ ከፍተኛ ሊጉ እንዳይወርድ ስጋት እንዳለቸው ገልጸዋል፡፡
በሊጉ እስካሁን ካደረጋቸው 10 ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በአራቱ ደግሞ አቻ ሲለያይ በአራቱ ጨዋታዎች ተረትቷል፡፡ በዚህም በ10 ነጥብ እና በሶስት የግብ እዳ በ10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
በቡድኑ አባላት በኩል እንደ ጥሩ ነገር እየተጠበቀ የሚገኘው በመጪው ቅዳሜ (ከጨዋታው 1 ቀን በፊት) በይፉ የሚመረቀው የወልዲያው ሼክ መሀመድ አል አልአሙዲን ስታድየም ምርቃት ስነስርዓት ላይ የሚገኙት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ባለሀብት ሼክ መሀመድ አሊ አልአሙዲን በእለቱ ለክለቡ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ከገቡ የሚል ተስፋን ይዘው መጪውን ቅዳሜ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተያያዘ ዜና የወልዲያው አዲሱ ስታድየም በመጪው ቅዳሜ ጥር 6 ሼክ መሀመድ አል አሙዲንን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች በተገኙበት ከጠዋት 03:00 በሚካሄድ ዝግጅት ይመረቃል፡፡ አዲስ አበባ እና ወልድያ በሚገኙ የሚድሮክ ሰራተኞች መካከልም የወዳጅነት ጨዋታ ይደረጋል፡፡ በማግስቱ እሁድ ደግሞ ወልድያ ከ ድሬዳዋ ከተማ በሚያደርጉት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ታሪካዊ ጨዋታ ስታድየሙ በይፋ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡