የጋቦን 2017 ተሳታፊዎች ፕሮፋይል | ሞሮኮ [የአትላስ አናብስት]

ሞሮኮ በ2015 የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ሃገር ሆና ብትመረጠም በወቅቱ በምዕራብ አፍሪካ ጥቂት ሃገራት በነበረው የኢቦላ በሽታ ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሩን ባለማዘጋጀቷ ከካፍ ቅጣት ቢተላለፍባትም ቅጣቱ ተግባራዊ ሳይሆን ለ2017 የአፍሪካ ዋንጫ በአዲስ አሰልጣኝ ለጨዋታ ቀርበዋል፡፡

በ1976 ኢትዮጵያ ላይ በተስተናገደው የአፍሪካ ዋንጫ ቻምፒዮን የቻሉት የአትላስ አንበሶቹ የሰፋ የአፍሪካ ዋንጫ ልምድ ቢኖራቸውም ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን ከምድባቸው ማለፍ ሲሳናቸው ተስተውሏል፡፡ ሞሮኮ በ2004 ለፍፃሜ ብትደረስም በቱኒዚያ ተሸንፋ ዋንጫ አጥታለች፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት፡ 15

ውጤት፡ አንድ ግዜ አፍሪካ ቻምፒዮን (1976)

አሰልጣኝ፡ ሄርቬ ሬናርድ

ሞሮኮ በምድብ ሶስት ከካቻምና አሸናፊዋ ኮትዲቯር ፣ ዲ.ሪ. ኮንጎ እና ቶጎ ጋር ተመድባለች፡፡ ፈረንሳዊው የ48 ዓመት አሰልጣኝ ሄርቬ ሬናርድ የሞሮኮ አሰልጣኝ ነው፡፡ ሬናርድ ካለፉት ሶስት የአፍሪካ ዋንጫዎች ሁለቱን ማሸንፍ ችሏል፡፡ የአሰልጣኝነት ህይወቱን የክላውድ ለርዋ ምክትል በመሆን የጀመረው ሬናርድ በ2012 ዛምቢያን እንዲሁም በ2015 ኮትዲቯርን የአፍሪካ ቻምፒዮን አድርጓል፡፡ ሞሮኮ በባዱ ዛኪ እየተመራች ወሳኝ የሆኑትን የማጣሪያ ጨዋታዎች ያደረገች ሲሆን ሬናርድ ከመጣ በኃላ በነበሩት ጨዋታዎች የቡድኑን መከላከል እና የማጥቃት መሰረት በመስራት ላይ ተጠምዶ ቆይቷል፡፡ ምንም እንኳን ሞሮኮ በሁለት የዓለም ዋንጫ ማጣሪዎች ግብ ሳታስቆጥር ብትወጣም አዲስ ፈተናን መጋፈጥ የሚወደው ሬናርድ በአፍሪካ ዋንጫው የተለየ ነገር ለማሳየት ያስባል፡፡

ተስፋ

ሞሮኮ አስቀድማ ወደ አፍሪካ ዋንጫ በማለፏ የቡድኑ የአሰልጣኞች ስታፍ ቀሪ ጊዜያቸውን የቡድኑን የተከላካይ ስፍራ በማጠናከር ላይ ተጠምደው ታይተዋል፡፡ ይህም በአፍሪካ ዋንጫ የተሻለ የተከላካይ ስፍራ ይዛ እንድትቀርብ ያስችላታል፡፡  ቡድኑ ተጋጣሚዎቹን በፍጥነት የመልመድ ባህሪን እያሳየ ይገኛል፡፡ ወሳኝ በሆነው የምድብ ማጣሪያ ይህ ሞሮኮን ሊጠቅም ይችላል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ ስኬትን በቅርብ ግዜያት ሁለቴ ማጣጣም የቻለው ሬናርድን መያዟ ሌላው የሞሮኮ ተስፋ ነው፡፡ ሬናርድ በውድድሩ ላይ ከ9 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው ሲሆን የመሪነት ብቃቱን የአትላስ አንበሶቹን በምድብ ማጣሪያው ለማሸነፍ ፈታኝ ሃገር ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡

ስጋት

ቡድኖች ወሳኝ ተጫዋች ሊጎዳባቸው ይችላል፡፡ ቢሆንም የጉዳት መጠኑ ብዛት ባለቸው ወሳኝ ተጫዋቾች ላይ ሲሆን ደግሞ ያለው ተፅእኖ ሰፊ ነው፡፡ የኑስ ቤልሃንዳ፣ ኑረዲን አመርባት፣ ሶፊያን ቡፋል እና ኦስማን ታናንን የመሳሰሉ ጥሩ የመሃል ሜዳ ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ውጪ ናቸው፡፡ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ማጣታ ለሞሮኮ ነገሮች አስቸጋሪ ያደርጋል፡፡ የመሃል አጥቂ ላይ ክፍተት ይታይበታል፡፡ በተለይ የሱፍ ኤል አረቢ በብቃቱ ጫፍ ላይ ሲገኝ እና ከጭራሱ ሳይኖር የሞሮኮ የግብ ማስቆጠር አቋምም በዚያው ልክ ይዋዥቃል፡፡ ይህ የተደጋጋመ ችግር ሳይፈታ ወደ ውድድር ከገቡ የጋቦን ቆይታቸው ያጠራጥራል፡፡

የሚጠበቁ ተጫዋቾች

ሞሮኮ ወሳኝ ተጫዋቾቻ በመጎዳታቸው ሊጠበቁ የሚችሉት ተጫዋቾች ጥቂት ናቸው፡፡ በአቡዳቢው ሃያል ክለብ አል-ጀዚራ የሚጫወተው ሙባሩክ ቦሱፋ በአማካይ ስፍራ ላይ ይጠበቃል፡፡ ልምድ ያለው ታታሪው አማካይ ካሪም ኤል-አህመዲ ለሃገሩ ትልቅ ግልጋሎት ሊሰጥ ይችላል፡፡ የተከላካይ ስፍራው በትልቅ ደረጃ በሚጫወተው መህደ ቤንአተያ ይመራል፡፡ ጥሩ የመከላካል ያለው ቤንአቲያ ብቃቱ በውድድሩ ወቅት ካልወረደ ለአትላስ አንበሶቹ ወደፊት ጉዞ ላይ ወሳኝ ይሆናል፡፡ የሞሮኮን የግብ ማግባት ችግር ሙሉ ለሙሉ ባይቀርፍም የሱፍ ኤል አረቢ የተዋጣለት ግብ አዳኝ ነው፡፡ ኤል አረቢ ትከሻ ላይ ያለው ጫና ከባድ ቢሆንም በካታር የሚጫወተው የፊት መስመር ተሰላፊ የተጋጣሚ ሃገራት ሊጠነቀቁት የሚገባ ተጫዋች ነው፡፡

የማጣሪያ ጉዞ

ሞሮኮ በምድብ ስድስት ከኬፕ ቨርድ፣ ሊቢያ እና ሳኦቶሜ እና ፕሪንስፕ ጋር ተመድባ ነበር፡፡ ካደረገቻቸው ስደስት ጨዋታዎች አምሰቱን ስታሸንፍ ለሊቢያ ጋር አንድ ግዜ አቻ ተለያይታለች፡፡ አስር ግብ አስቆጥራ በአንፃሩ አንድ ግብ ብቻ አስተናግዳ በ16 ነጥብ የምድቡ መሪ በመሆን ጨዋታዋን ጨርሳለች፡፡

ሙሉ ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

ያሲን ቦኖ (ጂሮና/ስፔን)፣ ሙኒር ኤል-ካጆኢ (ኑማንሲያ/ስፔን)፣ ያሲን ኤል-ካሮቢ (ሎኮሞቲቭ ፕሎዲቭ/ብልጋሪያ)

ተከላካዮች

መህዲ ቤንአታያ (ጁቬንቱስ/ጣሊያን)፣ ሃምዛ መንዲል (ሊል/ፈረንሳይ)፣ ፉአድ ሻፊቅ (ዲዮን/ፈረንሳይ)፣ ማኑኤል ዳ ኮስታ (ኦሎምፒያኮስ/ግሪክ)፣ ጋኔም ሳኢስ (ዎልቨርሃምፕተን/እንግሊዝ)፣ አሚን አቱቺ (ዋይዳድ ክለብ አትሌቲክ/ሞሮኮ)

አማካዮች

ካሪም ኤል-አህመዲ (ፌይኖርድ ሮተርዳም/ኒዘርላንድስ)፣ፋይሰይ ፋጃር (ዲፖርቲቮ ላ ኮሮኛ/ስፔን)፣ ካሊድ ቦታይብ (ስታርስቦርግ/ፈረንሳይ)፣ ሙባረክ ቦሶፋ (አል-ጀዚራ ኢማራቲ/የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች)፣ የሱፍ ቤንአሰር (ናንሲ ሎሬን/ፈረንሳይ)፣ ነቢል ድራር (ሞናኮ/ጋና)፣ ሙኒር ኦባዲ (ሊል/ፈረንሳይ)፣ መህዲ ካርሴላ (ግራናዳ/ስፔን)፣ ኦማር ኤል-ካዱሪ (ናፖሊ/ጣሊያን)፣ ፋይሰል ሬራስ (ሃርትስ/ስኮትላድ)

አጥቂዎች

የሱፍ ኤል-አረቢ (ሉክዊያ/ካታር)፣ የሱፍ ኢን-ነስሪ (ማላጋ/ስፔን)፣ አዚዝ ቦአዶዝ (ሴንት ፖሊ/ጀርመን)፣ ራሺድ አሊዊ (ኒምስ/ፈረንሳይ)

ሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞዋን ዲ.ሪ. ኮንጎን ዛሬ በመግጠም ትጀምራለች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *