ፕሪሚየር ሊግ ፡ ኢትዮጵያ ቡና ከዳሽን ጋር ነጥብ ተጋራ

በ17ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በተደረገ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ዳሽን ቢራን አስተናግዶ ካለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡

11፡30 በተጀመረው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናዎች በሻኪሩ እና ቢንያም አሰፋ አማካኝነት የግብ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ ያመሸው የዳሽን ግብ ጠባቂ ደረጄ አለሙ አክሽፎባቸዋል፡፡

ከጨዋታው በኋላ የዳሽን ቢራው አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ተጫዋቾቻቸው ሰአት ለማባከንና የአቻ ውጤትን አስጠብቀው ለመውጣት መጫወታቸውን አስተባብለዋል፡፡ ‹‹ አቻ ለመውጣት ሳይሆን በመልሶ ማጥቃት ግብ አስቆጥረን ለማሸነፍ ነበር የገባነው፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ ብልጫ ቢወሰድብንም ወደ ግብ በመድረስ እኛ የተሸልን ነበርን፡፡ በ2ኛው አጋማሽ ደግሞ የሲስተም ለውጥ አድርገን ከቡና በተሻለ ተንቀሳቅሰናል፡፡ በአጠቃላይ በአልሸነፍ ባይነት ቡናን በበርካታ ደጋፊዎቹ ፊት ነጥብ አስጥለን በመመለሳችን ደስተኞች ነን፡፡ ›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የቡናው አጥቂ አቢኮዬ ሻኪሩ በበኩሉ ‹‹ ዛሬ እድለኞች አልነበርንም፡፡ ዳሽኖች ለመጫወት ሳይሆን ሰአት ለመግደል ነው አዲስ አበባ የመጡት ›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *