የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት 2ኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1-0 በማሸነፍ የሊጉን አናት ተቆናጧል፡፡
ጨዋታው የተጠበቀውን ያህል እንቅስቃሴ ያልታየበት ሲሆን በተለይም የመጀመርያው አጋማሽ አሰልቺ የሚባል እንቅስቃሴ አስመልክቶናል፡፡
በዚሁ የመጀመርያ አጋማሽ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ በሁለቱም በኩል መመልከት ያልቻልን ሲሆን በ9ኛው ደቁቃ ራምኬል ሎክ ግብ ጠባቂው ሱሌይማን አቡ በአግባቡ ማራቅ ያልቸቻለውን ኳስ ሞክሮ የግቡ ቋሚ ከመለሰበት ውጪ የሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ በሚገኙ ተጫዋቾች ምክንያት ሲበላሽ ተስተውሏል፡፡
ከመጀመርያው በመጠኑ የተሻለ እንቅስቃሴ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ የግብ ሙከራዎች እና ቀይ ካርዶች አስመልክቶናል፡፡
53ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መሰመር አበባው ቡታቆ ያሻማውን ኳስ አዳነ ግርማ ሲገጨው በሱሌይማን አቡ እግሮች መሃል አልፋ የፈረሰኞቹን የድል ግብ ሆናለች፡፡ የኳሱ ፍጥነት ጠንካራ ባለመሆኑ የግብ ጠባቂው ስህተት ኤሌክትሪክን ዋጋ ያስከፈለ ሆኗል፡፡
ከግቡ መቆጠር በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሳላዲን ሰኢድን በአማካዩ ያስር ሙገርዋ ቀይሮ በማስገባት የማጥቃት እንቅስቃሴውን ይበልጥ ቢያጠናክርም ፤ ኢትዮ ኤሌክትሪኮችም በሃይሉ ተሻገር እና ሙሉአለም ጥላሁንን ቀይረው በማስገባት የአቻነት ጎል ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው ቢንቀሳቀሱም ግልጽ የግብ ማስቆጠር እድሎች መፈጠር ሳይችሉ ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ የቅዱስ ጊዮርጉሰ አብዱልከሪም ንኪማ እና የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ተስፋዬ መላኩ በፈጠሩት እሰጥ እገባ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች ወደ ድል የተመለሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሊጉ አናት ሲመለስ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 11ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡