ዛሬ በአርባምንጭ ከተማ እና ሲዳማ ቡና መካከል የተደረገው የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ጨዋታ በአርባምንጭ ከተማ የበላይነት ተጠናቋል፡፡
ጨዋታው 35° በሆነ ሞቃታማ አየር ውስጥ በምትገኘው አርባምንጭ መደረጉ ለሚጫወትም ፣ ለተመልካችም አስቸጋሪ ቢሆንም ጨዋታው የደርቢ ባህርያት የሆኑት እልህ ፣ አልሸነፍ ባይነት እና ኃይል የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ የተስተዋለበት ፣ ግሩም ግቦች የተስተናገዱበት ፣ አስገራሚ ትይንቶች በጨዋታው መሀል የተመለከትንበት ጨዋታ ሆኖ አልፏል፡፡
በሲዳማ ቡና ማልያ የቀድሞ ክለባቸውን የገጠሙት አበበ ጥላሁን አንተነህ ተስፋዬ ትርታዬ ደመቀ ሙሉአለም መስፍን ለሕዝቡ ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ እጅ በመንሳት ሰላምታ ሲያቀርቡ ተመልካቹም ከመቀመጫው በመነሳት በአፀፋው የሰጣቸው ምላሽ ከጨዋታው አስቀድሞ የነበረ ትይንት ነበር፡፡
የዕለቱ ዳኛ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በመሩት ጨዋታ የመጀመርያዎቹ 15ኛው ደቂቃዎች ኳሶች በሚገባ የታሰበለት አላማ የማይደርሱበት እንዲሁም ኳሶች የሚባክኑበት የመጠናናት እንቅስቃሴ ሲስተዋል በሁለቱም በኩል በነበረው ኃይል የተቀላቀለበት አጨዋወት ምክንየያዥ በተደጋጋሚ ጨዋታው ሲቆራረጥ ነበር፡፡
18ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን መንፈስ የሚቀይር ጎል ታደለ መንገሻ አስቆጥሯል፡፡ ታደለ ከወድሜነህ ዘሪሁን የተቀበለውን ኳስ የበረኛውን አቋቋም በማየት ከሳጥን ውጭ በመምታት አስቆጥሮ አርባምንጭን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡
ከዚህ ጎል መቆጠር በኋላ ጨዋታው ተጋግሎ ሲቀጥል ሲዳማ ቡናዎች አቻ ሊሆኑ የሚችሉበትን አጋጣሚ ትርታዬ ደመቀ ሞክሮ ግብ ጠባቂው አንተነህ መሳ እንደምንም አድኖበታል፡፡
26ኛው ደቂቃ ላይ በአርባምንጭ በኩል የጨዋታው ልዮነት ፈጣሪ የነበረው ወድሜነህ ዘሪሁን በድጋሚ ለገብረሚካኤል ያዕቆብ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ገ/ሚካኤል ወደ ጎልነት በመቀየር የአርባምንጭን መሪነት በሁለት ማስፋት ችሏል።
ከ30ኛው-40ኛው ደቂቃ ድረስ የጨዋታውን እንቅስቃሴ ሊያቋርጥ የሚችል ሁለት አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል፡፡ በ32ኛው ደቂቃ ላይ የቀይ መስቀል ህክምና ሰጪ አባላት በሜዳው ባለመገኘታቸው ክርክር አስነስቶ ለሁለት ደቂቃ ሲቋረጥ በድጋሚ ጨዋታው ቀጥሎ 36ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ቀይ መስቀል ባለመምጣቱ በሚል ጨዋታው ተቋርጦ ቀይ መስቀል ሲመጣ ጨዋታው ካቆመበት መቀጠሉ አግራሞትን ጭሯል፡፡
40ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ላይ የተሰራውን ጥፈት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፅም ቅጣት ምት አበበ ጥላሁን የቀድሞ ክለቡ ላይ በማስቆጠር ጨዋታው በአርባምንጭ 2-1 መሪነት የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቋል
በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ ተጋግሎና ተሟሙቆ ይቀጥላል ተብሎ ቢጠበቅም አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ እያለ ተጉዟል፡፡ ሲዳማ ቡናዎች አሸንፎ ለመውጣት የተከላካይ ቁጥራቸውን በመቀነስ የማጥቃት ቁጥራቸውን ቢያበዙም ምንም መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ይልቁንም የሲዳማ ቡና ተከላካይ ክፍል መሳሳቱን በመጠቀም አርባምንጮች በተደጋጋሚ ወደ ሲዳማ የጎል ክልል መድረስ ችለዋል፡፡ 76ኛው ደቂቃ ላይም ፀጋዬ አበራ የግል ብቃቱን በመጠቀም ተከላካዮችን አልፎ የአርባምንጭን መሪነት ወደ አሸናፊነት ያሸጋገረች ግብ አስቆጥሯል፡፡
በጨዋታው የተከሰተው የዕለቱ ረዳት ዳኛ የነበሩት አስቻለው ወርቁ ጉዳት አጋጥሟቸው የህክምና እርዳታ እስኪያገኙ የተወሰነ ደቂቃ ጨዋታው መቋረጡ ልዩ ክስተት ነበር ።
ከ80ኛው ደቂቃ በኋላ በቀሩት ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች ፀጋዬ ባልቻ ከሚያደርገው ጥረት በቀር ትርጉም አልባ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን በአንፃሩ ባለ ሜዳዎቹ አርባምንጮች ውጤት ለማስጠበቅ በጥንቃቄ ጨዋታውን ተቆጣጥረው በሜዳቸውና በደጋፊያቸው ፊት 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ጣፋጭ ድል አስመዝግበዋል፡፡
በመጨረሻም. . .
የአርባምንጭ ሜዳ ለጨዋታ አመቺ ካለመሆኑ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ እንክብካቤ ካልተደረገለት ወደፊት እግር ኳስ ጨዋታ ሊያስተናግድ እንደሚቸገር ታዝበናል፡፡ የሚመለከተው አካልም ትኩረት ሊያደርግበት እንደሚገባ ለመጠቆም እንወዳለን፡፡