ድሬዳዋ ከተማ አጥቂ ሲያስፈርም የተከላካዩንም ውል አራዝሟል

ብርትካናማዎቹ በወልቂጤ ከተማ ዓምና የተጫወተውን አጥቂ የግላቸው ሲያደርጉ የመስመር ተከላካያቸውንም ውል ለተጨማሪ ዓመት አድሰዋል፡፡

ለ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በሀዋሳ እየሰራ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ራሱን ከሊጉ መጀመር አስቀድሞ ለመፈተሽ ይረዳው ዘንድ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ ሲካፈል የነበረ ሲሆን ክለቡ አሁንም ክፍተት አለብኝ ባለው ቦታ ላይ አጥቂው ሄኖክ አየለን የግሉ ሲያደርግ የመስመር ተከላካዩ ያሲን ጀማልን ውልም አድሷል፡፡

አጥቂው ሄኖክ አየለ በአንድ ዓመት ውል ከሰአታት በፊት ለብርትካናማዎቹ ፊርማውን አኑሯል። የቀድሞው የደቡብ ፖሊስ ፣ አዳማ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና ፣ ጌዲኦ ዲላ ፣ ሀዋሳ ከተማ እንዲሁም ወደ ቀድሞ ክለቡ ወልቂጤ ከተማ በድጋሚ በመመለስ የተጠናቀቀውን አመት ያሳለፈው አጥቂው ማምሻውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን በመገኘት የአንድ ዓመት ውሉን በይፋ ፈርሟል።

ድሬዳዋ ከተማ ከሄኖክ አየለ በተጨማሪ የቀኝ መስመር ተከላካዩን ያሲን ጀማልን ውል አራዝሟል፡፡ ከታችናው ቡድን አንስቶ የምስራቁን ክለብ ያገለገለው ያሲን የአንድ ዓመት ውል መፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።