ወልቂጤ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ

በሀዋሳ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እያከናከነ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል፡፡

በሀዋሳ ከተማ በሚገኘው ኬርኦውድ ኢንተርናሽል ሆቴል ማረፊያቸውን በማድረግ ለ2014 የውድድር ዘመን የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው መሪነት በደቡብ ኢትዮጵያ ኮሌጅ ሜዳ እየሠሩ የሚገኙት ወልቂጤ ሁለት ተጨማሪ አዳዲስ ተጫዋቾችን በአንድ ዓመት ውል ወደ ክለቡ መቀላቀላቸውን አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል፡፡

አበባው ቡጣቆ ወደ ወልቂጤ ከተማን ተቀላቅሏል፡፡ የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ አህሊ ሸንዲ እንዲሁም የደቡብ ፖሊስ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የነበረው የግራ መስመር ተከላካዩ ያለፈውን የውድድር ዓመት ያለ ክለብ ያሳለፈ ሲሆን ከወልቂጤ ከተማ ጋር ከሰሞኑ ልምምድ በመስራት ቆይቶ ለአንድ ዓመት ቡድኑን ተቀላቅሏል።

የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋቹ አብረሃም ታምራት ወልቂጤን የተቀላቀለ ሌላው ተጫዋች ነው። ከዚህ ቀደም ለወልቂጤ ከተማ የተጫወተው ተጫዋቹ ለደቡብ ፖሊስ ፣ ደደቢት እና የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት ደግሞ በጅማ አባጅፋር ያሳለፈ ሲሆን ለቀጣዩ ዓመት ደግሞ ወደ ቀድሞ ክለቡ ወልቂጤ ከተማ ተመልሷል።