አስቻለው ታመነ ስለ ቻምፒዮንስ ሊጉ እና ወደ ቀድሞ አቋሙ ስለመመለሱ ይናገራል

የአምናው የፕሪምየር ሊግ ኮከብ አስቻለው ታመነ ከቀዝቃዛ አጀማመር በኋላ ወደ ቀድሞ አቋሙ እየተመለሰ ይገኛል፡፡ ቡድኑ እሁድ/ሰኞ ባደረገው የቻምፒየንስ ሊግ የመልስ ጨዋታ ኮት ዲ ኦር ላይ የ3-0 ድል ሲያስመዘግብ አንድ ጎል ማስቆጠርም ችሏል፡፡ አስቻለው ስለ ቻምፒየንስ ሊጉ እና ስለወቅታዊ አቋሙ ከዳንኤል መስፍን ጋር ያደረገውን አጠር ያለ ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡


አምና የሊጉ ኮከብ ተጫዋች ሆነህ መመረጥህ ይታወቃል ፣ በዘንድሮ አመት እንቅስቃሴህ ላይ ግን መቀዛቀዝ አሳይተሃል። ለዚህ እንደምክንያት የምትጠቅሰው ምንድነው?

ዘንድሮ ሊጉ ሲጀምር የመጀመርያዎቹ አራት ጨዋታዎች አምልጠውኝ ነበር። አምና በጥሎ ማለፍ ላይ ባየሁት ቀይ ካርድ ምክንያት በመቀጣቴ አልተጫወትኩም ፤ ያ መሆኑ ወደ ጨዋታ ስመለስ በተወሰነ መልኩ ከብዶኝ ነበር። ኪሎዬም ትንሽ ጨምሮ ስለነበር የአካል ብቃቴ እስኪስተካከልና ራሴን እስካገኝ ድረስ ትንሽ ተቸግሬ ነበር። ከዚህ ሁኔታ በተጨማሪ እጫወትበት የነበረው ቦታ ከተለመደው ቦታዬ ውጭ የመስመር ተከላካይ መሆኑ ሌላው ምክንያት ነበር። ያም ቢሆንም በአሁን ወቅት ራሴን ከሁኔታዎች ጋር አላምጄ ወደ ጥሩ አቋሜ ተመልሻለው።

አሁን በፕሪሚየር ሊጉ 1ኛ ዙር የመጨረሻ ሳምንታትም ሆነ በካፍ ቻምፒየንስ ሊጉ ለፈረሰኞቹ ጥሩ አገልግሎት እየሰጠህ ትገኛለህ፡፡ ይህን እንዴት ትገልፀዋለህ ?

ከአሰልጣኞቹና ከክለቡ አመራሮች ጋር በመነጋገር ወደ ቦታዬ መመለሴ ምቾት ተሰምቶኛል፡፡ አቋሜንም በሚገባ እያሳየው ጥሩም እየተንቀሳቀስኩ መሆኔን ብዙዎች እየነገሩኝ ነው። ትክክለኛ ቦታዬን አግኝቼ በመጫወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ እንግዲህ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ቡድን ሊወጣው የሚችል ስብስብ ያለው ክለብ ነው። በየቦታው አማራጭ የሚሆኑ ጠንካራ ተጨዋች አሉ ፤ ያለህን ቦታ ለማስጠበቅ ልምምድህን ጠንክረህ መስራት አለብህ ከዚህ በኋላም በቦታዬን በማስጠበቅ ቋሚ ሆኖ ለመጫወት ጠንክሬ እሰራለው፡፡

 አምና በቻምፒየንስ ሊጉ  ከቲፒ ማዜምቤ ጋር በተደረገው ጨዋታ በራስህ ላይ ጎል አስቆጥረሀል፡፡ እሁድ ደግሞ ኮት ዲኦር ላይ የመጀመርያ የኢንተርናሽናል ጎልህን አስቆጥረሀል. . .

እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች በእግር ኳስ የሚያጋጥሙ ነገሮች ናቸው፡፡ ማለትም በጨዋታ ጥሩ ተንቀሳቅሰህ ቡድንህን ትጠቅማለህ ፤ አልያም መጥፎ ቀን አሳልፈህ ቡድንህን ትጎዳለህ፡፡ አምና የሆነውም ይሄ ነው ፤ በወቅቱም ይህ በመሆኑ በጣም አዝኜ ነበር፡፡

እኔ ተከላከይ በመሆኔ የመጀመርያ ስራዬ መከላከል ነው። ብዙ ጎል ማስቆጠር ባይጠበቅብኝም በሚገኙ አጋጣሚዎች በአመት ሦስት እና አራት ጎል ማስቆጠር መቻል ለተከላካይ መስመር ተጫዋች ጥሩ ነው። እሁድ ጎል በማግባቴ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ የመጀመርያ ኢንተርናሽናል ጎሌም ነው። ቤተሰቦቼ በጠቅላላ ጨዋታውን ለመከታተል በስታድየም ተገኝተው የነበረ በመሆኑ በቤተሰቦቼ ፊት ጎል በማስቆጠሬ ደስታዬን እጥፍ ድርብ አድርጎታል።

በቀጣይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በአፍሪካ መድረክ ምን ታልማለህ?

በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግም ሆነ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ላይ ጥሩ እንጓዛለን ብዬ አስባለው፡፡ የሊጉ አጀማመራችን ጥሩ የነበረ ቢሆንም መሀል ላይ ቡድናችን ጥሩ አቋም ላይ አልነበረም፡፡ አሁን በጥሩ ቅርፅ ላይ ይገኛል ፤ ይህን አጠናክረን እንቀጥላለን። በአፍሪካ መድረክም አጀማመራችን ጥሩ ነው፡፡ በድምር ውጤት 5-0 በማሸነፍ ጉዟችንን በጥሩ ውጤት ጀምረናል፡፡ በ1ኛው ዙር የሚገጥመንን ቡድን (ኤሲ ሊዮፓርድስ) አውቀናል፡፡ ምድብ ድልድል ውስጥ ለመግባት የሚያስችለንን ውጤት ለማስመዝገብ ጠንክረን እንሰራለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *