የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የምድብ ሁለት ጨዋታዎች ውሎ

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የምድብ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ባህር ዳር ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ እና ፋሲል ከነማን በተመሳሳይ 3-0 በሆነ ውጤት ረተዋል።

ባህር ዳር ከተማ 3-0 አዳማ ከተማ (8:00)

ስምንት ሰዓት ላይ የጀመረው ጨዋታው በባህር ዳር 3-0 የበላይነት ተጠናቋል።

የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የጀመሩት ባህር ዳር ከተማዎች በአንፃራዊነት በተሻለ የኳስ ቅብብል ወደ ጎል ለመድረስ ሲጥሩ ታይቷል። አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው ፈጣን የማጣቃት እንቅስቃሴ ወደ ግብ ለማምራት ቢሞክሩም እምብዛም ፍሬያማ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በጨዋታው ጅማሮ ላይ ግን ጥሩ ጥቃት ፈፅመው መክኖባቸዋል።

በ16ኛው ደቂቃ ላይ እጅግ የሰላ ጥቃት ያደረጉት ባህር ዳሮች በጨዋታው መሪ የሆኑበትን ኳስ ከመረብ አሳርፈዋል። ግቡ ከመቆጠሩ በፊት ግን ዓሊ ሱሌይማን ተከላካዮችን አምልጦ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ የሞከረው ኳስ የግብ ዘቡ ሴኩባ ካማራ ሲመልሰው ፉዐድ ፈረጃም አግኝቶት ወደ ግብ ልኮት ነበር። ነገርግን ቁመታሙ ግብ ጠባቂ ኳሱ መረብ ላይ እንዳያርፍ አድርጎታል። በተጠቀሰው ደቂቃ ግን ካማራ ወደ ውጪ ያወጣውን ኳስ በመዓዘን ምት ወደ ግብነት ለመቀየር የጣሩት የጣና ሞገዶቹ በግራ መስመር ተከላካያቸው አህመድ ረሺድ አማካኝነት ግብ አስቆጥረዋል።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ የተቸገሩት አዳማዎች ፈጣኖቹን የባህር ዳር አጥቂዎች መቆጣጠር ተስኗቸው በተደጋጋሚ ሲፈተኑ ተስተውሏል። በ36ኛው ደቂቃም በላላ የመከላከል አጨዋወት ሁለተኛ ጎል አስተናግደዋል። በዚህም ኤርትራዊው የቡድኑ አዲስ ተጫዋች ዓሊ ሱሌይማን ፍጥነቱን እና የቴክኒክ ብቃቱን ተጠቅሞ ግብ አስቆጥሯል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በጨዋታው ያላቸውን ተስፋ ለማለምለም መታተር የያዙት አዳማዎች እጅግ የሰላ ጥቃት ፈፅመው መክኖባቸዋል። በዚህም አጋማሹ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው አብዲሳ ጀማል ከመሐል የተላከለትን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ መትቶት የመጀመሪያ የጠራ የግብ ሙከራ ለቡድኑ ቢያደርግም ከሽፎበታል።

በሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት ተሻሽለው ወደ ሜዳ የገቡ የሚመስሉት አዳማ ከተማዎች ገና አጋማሹ በተጀመረ በአምስተኛው ደቂቃ ድንቅ ሙከራ አድርገው ነበር። በዚህም በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ሙከራ ያደረገው አብዲሳ በዚህ አጋማሽ ደግሞ የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ጥቃት ፈፅሞ ነበር። ነገር ግን የግብ ዘቡ አቡበከር ኑሪ አድኖበታል። በመጀመሪያው አጋማሽ ሲያደርጉ የነበሩትን ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ቀነስ ያደረጉት ባህር ዳሮች በ67ኛው ደቂቃ ሌላ ያለቀለት የግብ ማግባት አጋጣሚ ፈጥረው ነበር። በዚህም ዓሊ ከግርማ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ከአንድ የተገናኘበትን ኳስ ተቀብሎ በቀጥታ ወደ ግብ ቢመታውም ዒላማን ሳያገኝ ቀርቶ ወደ ውጪ ወጥወጥቶበታል።

ሦስት ደቂቃዎች በኋላም በእንቅስቃሴ ተስቦ አዳማ የግብ ክልል የተገኘው የመሐል ተከላካዩ ሰለሞን ወዴሳ ጥሩ ኳስ ወደ ግብ የመታ ቢሆንም በርካታ ያለቀላቸውን ኳሶች ሲያድን የነበረው ካማራ መልሶታል። ጨዋታው ቀጥሎ 78ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ባህር ዳር ከተማዎች መሪነታቸውን ወደ ሦስት ከፍ ያደረጉበትን ጎል አግኝተዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ተመስገን ደረሰ ከዓሊ የደረሰውን ኳስ ከመረብ ላይ አዋህዶታል። በጨዋታው የማስተዛዘኛ ጎል ለማግኘት የሞከሩት አዳማዎች በጭማሪው ደቂቃ ዳዋ በሞከረው ኳስ አንድ ጎል ሊያገኙ ቢቃረቡም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ጨዋታው በባህር ዳር ከተማ ሦስት ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተመረጠው የባህር ዳር ከተማው አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን ከአሠልጣኝ ወርቁ ደርገባ እጅ የ12 ሺ ብር እና የዋንጫ ሽልማቱን ተረክቧል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 ፋሲል ከነማ (10:00)

የዕለቱ ተጠባቂ መርሐ-ግብር የሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ እጅግ በርካታ ደጋፊዎች በተገኙበት ተከናውኖ ጠንካራ ፉክክር አስመልክቷል። በጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ያደረጉትም የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ፋሲል ከነማዎች ናቸው። በዚህም በ11ኛው ደቂቃ በግራ መስመር ወደ ጊዮርጊስ የግብ ክልል በማምራት አስደንጋጭ ሙከራ በአቤል እያዩ አማካኝነት ሰንዝረው ዩጋንዳዊው የግብ ዘብ ቻርለስ ሉክዋጎ አድኖባቸዋል። ከደቂቃ በኋላም በተመሳሳይ መስመር በረከት ደስታ ኳስ እየገፋ ሄዶ የሞከረውን ኳስ በድጋሜ ሉክዋጎ ተቆጣጥሮታል።

በተቃራኒው ወደ ቀኝ መስመር ያደላ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የታዩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጨዋታው ሩብ ደቂቃ ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። በዚህም የቀኝ መስመር አጥቂው ፀጋዬ መላኩ እጅግ የተመጠነ ኳስ ወደ ሳጥን ሲያሻግር ራሱን ነፃ አድርጎ ሲጠብቅ የነበረው የቡድኑ አምበል ሀይደር ሸረፋ ጎል አድርጎታል።

ወደ ጨዋታው በቶሎ ለመመለስ ያሰቡ የሚመስሉት የአሠልጣኝ ሥዩም ከበደ ተጫዋቾች በ21ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ዮሐንስ በመታው የቅጣት ምት አቻ ሊሆኑ ነበር። ከዚህ የቆመ ኳስ በተጨማሪም በ37ኛው ደቂቃ ከወደ ቀኝ በኩል ሌላ የቅጣት ምት አግኝተው በበረከት ደስታ አማካኝነት ቢሞክሩትም ዒላማ ሳያገኙ ቀርተዋል። የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመሩት ሁለት ደቂቃዎች አጋማሽ ላይ ደግሞ ከቀኝ መስመር የተሻገረን ኳስ ፍቃዱ ዓለሙ ወደ ግብነት ሊቀይረው ጥሮ ወጥቶበታል። አጋማሹም በፈረሰኞቹ መሪነት ተጠናቋል።

አጋማሹ እንደተጀመረ መሪነታቸውን ለማስፋት ተግተው የተንቀሳቀሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሦሰት ተከታታይ ሙከራዎችን በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት አድርገው በመጨረሻም ተሳክቶላቸዋል። በዚህም በ48ኛው ደቂቃ የአጥቂ አማካዩ አላዛር ሳሙኤል ብቃቱን ያሳየበትን ጎል አስቆጥሩ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት አሳድጓል።

ገና ከመልበሻ ክፍል እንደወጡ ፈተና የጠናባቸው ዐፄዎቹ በ54ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ባሻማው እና የመሐል ተከላካዩ ከድር ኩሊባሊ በግንባሩ በሞከረው ኳስ የመጀመሪያ ጎል ሊያስቆጥሩ ነበር። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከሳጥን ውጪ ኳስ መቶ መረብ ላይ ሊያሳርፍ ነበር። 62ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ በድጋሜ ወደ ጊዮርጊስ የግብ ክልል በርከት ብለው በማምራት በአምበላቸው ሰዒድ ሀሰን አማካኝነት ሌላ ጥቃት ቢፈፅሙም ፍሬያማ ሳይሆኑ ተመልሰዋል።

የጨዋታውን የሀይል ሚዛን የተነጠቁ የሚመስሉት ፈረሰኞቹ ሁለተኛ ግብ ካገቡ በኋላ የማጥቃት ፍላጎታቸው ተቀዛቅዟ ታይቷል። በተቃራኒው ደግሞ ፋሲሎች ከጨዋታው የተሻለ ነገር ለማግኘት መንቀሳቀስ ቀጥለዋል። 73ኛው ደቂቃ ላይም ፍቃዱ እጅግ ጥሩ ኳስ ከመሐል ተሰንጥቆለት ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም ግብ ጠባቂው ሉክዋጎ እና የመስመር ተከላካዩ ሄኖክ ተጋግዘው ኳሱን ወደ ውጪ አውጥተውታል። ሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አስር ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ኦኪኪ አፎላቢ ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ መረብ ላይ ለማገናኘት ቢጥርም የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። ጊዮርጊሶች በበኩላቸው በ84ኛው ደቂቃ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት በፀጋዬ እና የአብስራ አማካኝነት ተከታታይ ሙከራዎችን አድርገው ነበር። ነገርግን የፀጋዬን ኳስ ግብ ጠባቂው ቴዎድሮስ ሲመልሰው የየአብስራ ኳስ ደግሞ ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቷል።

ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ ጥፋት ተሰርቶ የፍፁም ቅጣት ምት ያገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቶጎዋዊው አጥቂ እስማኤል አውሮ-አጎሮ አማካኝነት ወደ ግብነት ቀይረውት ጨዋታው ሦስት ለባዶ ጨርሰዋል።

የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተመረጠው የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካኝ ሀይደር ሸረፋ ደግሞ የዋንጫ እና የ12 ሺ ብር ሽልማቱን ከክብር እንግዳው ግርማ ሳህሌ (የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች) ተቀብሏል።