ማሊያዊው አጥቂ ብርቱካናማዎቹን በይፋ ተቀላቅሏል

ከሳምንታት በፊት ድሬዳዋ ከተማን ለመቀላቀል ተስማምቶ የነበረው ማሊያዊው አጥቂ በይፋ ለክለቡ ፊርማውን አኑሯል።

በአሠልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የሚመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች አዳዲስ ተጫዋቾችን በመቀላቀል በሀዋሳ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እንደጀመሩ ይታወቃል። ከሳምንታት በፊት እንደተገለፀውም ክለቡ ማሊያዊውን አጥቂ ማማዱ ሲዲቤን ለማስፈረም ተስማምተው ነበር። ቁመታሙ አጥቂም ከቀናት በፊት አዲስ አበባ በመግባት  በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በመገኘት በይፋ ለክለቡ ፊርማውን ማኖሩ ታውቋል።

2011 ላይ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የጅማ አባጅፋር ተጫዋች የሆነው ሲዲቤ አንድ ዓመት በክለቡ ከቆየ በኋላ ወደ ባህር ዳር ከተማ በማቅናት የእግርኳስ ህይወቱን ቀጥሎ ነበር። ከዛ ደግሞ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ወደ ሲዳማ ቡና በመሄድ ግልጋሎት የሰጠው አጥቂው ባለንበት ዓመት የምስራቁን ክለብ ለማገልገል የአንድ ዓመት ውል ፈርሟል።