መከላከያ የተጫዋቹን ውል አድሷል

በአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመሩት መከላከያዎች ከ17 ዓመት በታች ቡድናቸው ጀምሮ ሲያገለግላቸው የነበረውን አማካይ ውል አራዝመዋል።

ዛሬ በሚጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ላይ የሚሳተፉት መከላከያዎች የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ቢሾፍቱ ላይ ካከናወኑ በኋላ ለመዲናው ውድድር በትናንትናው ዕለት አዲስ አበባ ገብተዋል። ቡድኑ ትናንት አዲስ አበባ እንደገባም የአማካይ ተጫዋቹ አቤል ነጋሽን ውል በአንድ ዓመት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተገኝቶ ማራዘሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። ከ2008 ጀምሮ ከ17 ዓመት በታች አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ጦሩን ያገለገለው አቤል በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም ተጠርቶ መጫወቱ አይዘነጋም።

በተያያዘ ዜና በዛሬው የሲቲ ካፕ የመክፈቻ ጨዋታ የሚጫወተው መከላከያ ከቀናት በፊት ባወጣው ሀገር አቀፍ የምልመላ ማስታወቂያ ከተመለከታቸው ከ500 በላይ ታዳጊዎች አስራ ሁለቱን በመዲናው ውድድር እንደሚጠቀም ታውቋል። በዚህም ኪም ላም (ከጋምቤላ – በሀዋሳው የክልሎች ውድድር የተገኘ)፣ አብርሃም በላይነህ (ባህር ዳር)፣ ሚኪያስ ፀጋዬ (ሀረር)፣ ዮሐንስ መንግስቱ (አዲስ አበባ)፣ አቡበከር መሐመድ (አዲስ አበባ)፣ ሐብታሙ ጥጋቡ (ባህር ዳር ከተማ)፣ በረከት ወርቁ (ባህር ዳር ከተማ)፣ ትንሳኤ አዲስ (ባህር ዳር ከተማ)፣ ብሩክ ምትኩ (አዲስ አበባ ከተማ)፣ እንዳልካቸው ጥበቡ (አርባምንጭ) እና ኢብራሂም መሐመድ (አዲስ አበባ ከተማ) ከዋናው ቡድን ጋር በውድድሩ ተሳትፈው ጥሩ ግልጋሎት የሰጡትን በቢጫ ቴሴራ ወደ ዋናው ቡድን ለመቀላቀል እንደታሰበ ተጠቁሟል።