የ2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግ ዛሬ ተጠናቋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫውን ሲቀበል ሙገር ሲሚንቶ ደግሞ ወልድያን ተከትሎ ወደ ብሄራዊ ሊግ ወርዷል፡፡
ወደ ቦዲቲ ያቀናው ኤሌክትሪክ ወላይታ ድቻን 1-0 በማሸነፍ ለከርሞ በሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል፡፡ የኤሌክትሪክን የድል ግብ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች የኤሌክትሪክ ወሳኝ ተጨዋች መሆን የቻለው ሄይቲያዊው አማካይ ሳውረን ኦልሪስ ከመረብ አሳርፏል፡፡ የኤሌክተሪክን ድል ተከትሎ በተመሳሳይ ሰአት አዲስ አበባ ስታድየም ላይ መከላከያን ያሸነፈው ሙገር ሲሚንቶ ከኤሌክትሪክ በ3 ነጥቦች አንሶ ወደ ብሄራዊ ሊግ ወርዷል፡፡
ወደ ወልድያ የተጓዘው ኢትዮጵያ ቡና 2-2 አቻ ተለያይቷል፡፡ ወልድያዎች በማይክ ሰርጂ እና ወሰኑ ማዜ (ፍፁም ቅጣት ምት) ግቦች 2-0 መምራት ቢችልም ጋቶች ፓኖም እና ዮናስ ገረመው ኢትዮጵያ ቡናን አቻ አድርገዋል፡፡
አርባምንጭ ከነማ ወደ አዳማ ተጉዞ 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ይህ ሽንፈት ለአዳማ ከነማ በዘንድሮው የውድድር ዘመን የመጀመርያ የሜዳ ሽንፈት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር 2-2 አቻ ተለያይተዋል፡፡ ናይጄርያዊው አጥቂ ፊሊፕ ዳውዚ አንድ ግብ ቢያስቆጥርም የሳሚ ሳኑሚ 22 ግቦች ላይ ሳይደርስ የውድድር ዘመኑ ተጠናቋል፡፡
ሀዋሳ ላይ በሳምንቱ አጋማሽ አሰቃቂ ሽንፈት ያስተናገደው ሀዋሳ ከነማ ዳሽን ቢራን 4-2 በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን በድል ዘግቷል፡፡
የእለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በሆነው የአዲስ አበባ ስታድየም ፍልሚያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደደቢትን 1-0 በማሸነፍ የመዝጊያውን ስነስርአት በድል አድምቋል፡፡ ዘንድሮ በድንቅ አቋም ላይ የሚገኘው አማካዪ ምንተስኖት አዳነ የማሸነፍያዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫውን ሲረከብ የአመቱ ኮከቦች ፣ የፀባይ ዋንጫ እና በውድድር ዘመኑ መሳከላት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ሽልማት ተሰጥቶ የውድድር ዘመኑ በይፋ ተዘግቷል፡፡