የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ መመራት ከጀመረ ወዲህ የመጀመርያ ልምምዱን ዛሬ ጠዋት አድርጓል፡፡ አሰልጣኙ ትላንት በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ባስታወቁት መሰረት ዛሬ ቡድኑ ለ4 ተከፍሎ እርስ በእርሱ ተጋጥሟል፡፡ ከተመረጡት 44 ተጫዋቾች ውስጥ የሲዳማ ቡናዎቹ አብዱልከሪም መሃመድ እና ለአለም ብርሃኑ በጉዳት ምክንያት ከዛሬው የምርጫ ጨዋታ ውጪ የሆኑ ሲሆን በስብስቡ ውስጥ 3 ግብ ጠባቂዎች በመቅረታቸው የሙገሩ አቤል ማሞ በሁለቱም ጨዋታ ላይ ተሳትፏል፡፡
የመጀመርያው ግጥሚያ…
2፡55 ላይ የተጀመረው የመጀመርያው የእርስ በእርስ ፍልሚያ ላይ እያንዳንዱ ቡድን 10 ተጫዋቾች ያቀፈ ሲሆን አረንጓዴ እና ቢጫ ማልያ በመልበስ ግጥሚያቸውን አድርገዋል፡፡
በሁለቱ በኩል የተሰለፉት ተጫዋቾች የሚከተሉት ናቸው፡፡
አረንጓዴ መለያ – ታሪክ ጌትነት – ዘካርያስ ቱጂ – ኤፍሬም ወንድወሰን – ሞገስ ታደሰ – ሲሳይ ቶሊ – ታከለ አለማየሁ – ፍሬው ሰለሞን – ኤፍሬም ቀሬ – ብሩክ ቃልቦሬ – ተመስገን ተክሌ
ቢጫ መለያ – አቤል ማሞ – ግርማ በቀለ – ተስፋዬ በቀለ – በረከት ቦጋለ – ጋዲሳ መብራቴ – አስራት መገርሳ – ምንተስኖት አዳነ – ባዬ ገዛኸኝ – ታደለ መንገሻ – ቢንያም አሰፋ
በጨዋታው አረንጓዴ መለያ የለበሰው ቡድን 5-3 ሲያሸንፍ ተመስገን ተክሌ (57′ 83′) ፍሬው ሰለሞን (67′) እና ኤፍሬም ቀሬ (21′ 49′) የአረንጓዴውን ፣ ቢንያም አሰፋ (3′ 57′ ) እና ጋዲሳ መብራቴ (75′) ደግሞ የቢጫውን ቡድን ግቦችን አስቆጥረዋል፡፡
አማካዩ አስራት መገርሳ በጨዋታው 53ኛ ደቂቃ ላይ በጉዳት አቋርጦ ለመውጣት ሲገደድ ቀሪውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቢጫው ቡድን በጎዶሎ ተጨዋች ጨርሷል፡፡
ሁለተኛው ግጥሚያ . . .
4፡38 ላይ የተጀመረው ሁለተኛው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች 11 ተጫዋቾች ይዘው ግጥሚያውን አከናውነዋል፡፡ አንደኛው ቡድን ቢጫ መለያ ሲለብስ ሌላኛው ደግሞ አረንጓዴ/ቢጫ (stripe) መለያ ለብሰዋል፡፡
በሁለቱ በኩል የተሰለፉት ተጫዋቾች የሚከተሉት ናቸው
ቢጫ – አቤል ማሞ – ታጋይ አበበ – አዲሱ ተስፋዬ – ሙጂብ ቃሲም – ራምኬል ሎክ – ሳምሶን ጥላሁን – ጋቶች ፓኖም – ቴዎድሮስ በቀለ – በኃይሉ አሰፋ – አላዛር ፋሲካ – በረከት ይስሃቅ
አረንጓዴ/ቢጫ – ጀማል ጣሰው – ተካልን ደጀኔ – ሳላዲን በርጊቾ – አስቻለው ታመነ – አሸናፊ ሽብሩ – ሱራፌል ጌታቸው – ታፈሰ ሰለሞን – አስቻለው ግርማ – ኤፍሬም አሻሞ – ዮናታን ከበደ – ሙሉአለም ጥላሁን
በጨዋታው ቢጫ መለያ የለበሰው ቡድን 3-1 አሸንፏል፡፡ ለቢጫ መለያዎች ግቦቹን ራምኬል(49′) ፣ በኃይሉ (43′) እና አላዛር (20′) ሲያስቆጥሩ አሸናፊ ሽብሩ (26′) ለአረንጓዴ/ቢጫ ብቸኛዋን ግብ አስቆጥሯል፡፡
የመሃል ተከላካዩ ሳላዲን በርጊቾ በእረፍት ሰአት በስዩም ተስፋዬ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ በነገው እለትም እንደዛሬው እርስ በእርሱ ተጫውቶ አሰልጣኝ ዮሃንስ ያመኑባቸውን 23 ተጫዋቾች የሚመርጡ ሲሆን የቡድን መሪው አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ትላንት በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ባስታወቁት መሰረት ሽመልስ በቀለ እና ኡመድ ኡኩሪ ስብስቡን ሀሙስ ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሳላዲን ሰኢድ ክለቡ አል አህሊ ከክለብ አፍሪካን ጋር የሚያደርገው የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የሚሆን በመሆኑ እስከ ማክሰኞ ድረስ ቡድኑን ይቀላቀላል፡፡ ጌታነህ እና ዋሊድ አታ ደግሞ የክቦቻቸውን ምላሽ እየጠበቁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡