የጨዋታ ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው ተሸንፎ ከምድቡ መሰናበቱን አረጋግጧል

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ 5ኛ የምድብ ጨዋታ አአ ስታድየም ላይ የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ተሸንፏል፡፡ ወደ ሩብ ፍጻሜ የማለፍ ተስፋውም ጨልሟል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በቀይ እና ቢጫ ጨርቆች በሚገጣጠም (ሞዛይክ) ሙሉ ስታድየሙን አድምቀውት ለሜዳውም የተለየ ድባብ አላብሰውት ውለዋል፡፡

በመጀመርያው አጋማሽ የመጀመርያ ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ በተደጋጋሚ ወደ ግብ በመድረስ እና የግብ እድሎችን በመፍጠር የተሻለ ነበር፡፡ በተለይ በ5ኛው ደቂቃ በኃይሉ አሰፋ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ተከላካዩ ሞዳይስ ለማውጣት በማሰብ ጨርፎት የግቡን ቋሚ መትታ የወጣችው እንዲሁም  በ7ኛው ደቂቃ በኃይሉ ያሻማውን ኳስ ኦንያንጎ ሲያድነው በቅርብ ርቀት የነበረው ፕረሪንስ አግኝቶ በሚያስቆጭ መልኩ ያመከነው ኳስ ፈረሰኞቹ በጊዜ መሪ መሆን የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

የጨዋታው ከ10 ደቂቃ ከተገባደደ በኋላ እነግዶቹ ሰንዳውንሶች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡ ኳስን በዝግታ በማንሸራሸርም የጨዋታውን ፍጥነት ለማቀዝቀዝ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው እስከ መጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ድረስ ጊዮርጊስ ከርቀት ከሚሞከሩ አጋጣሚዎች በቀር ግልፅ የሚባል የማግባት አጋጣሚዎች እንዳያገኙ መግታት ችለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ስታድየም የመጫወቻ ሜደዳ ኳስን በአግባቡ ለማንሸራሸር አዳጋች ሆኖ የታየ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ኳስ ለመቀባበል የሚያደርጉት ጥረት በተደጋጋሚ በሜዳው ምክንያት ሲበላሽ ተስተውሏል፡፡

ጨዋታው በዚህ ሒደት ቀጥሎ የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአብዱልከሪም ኒኪማ እና ፕሪንስ አማካኝነት የግብ እድሎች መፍጠር ችለዋል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጫናም በ45ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቶ ፕሪንስ ከሳጥን ውጪ የሞከረውን ኳስ ተከላካዮች ሲደረቡበት በቅርብ የነበረው በኃይሉ አግኝቶ ሲመታ የሳንዳውንስ ተከላካይ ኳሷን በእጁ በመንካቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝቷል። ሆኖም የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ሳላዲን ሰኢድ መትቶ በቀድሞው የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ ዴኒስ ኦንያንጎ ከሽፏል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽም ያለ ግብ ተጠናቋል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በእንቅስቃሴ ረገድ ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የሚባል ነበር፡፡ በተለይም ሰንዳውንሶች ወደ ጊዮርጊስ የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመጠጋት የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል፡፡ በ64ኛው ደቂቃ ታኦ ከርቀት የሞከረውና ሮበርት ያደዳነበት ኳስም የሚጠቀስ ነበር፡፡

ጨዋታው በሁለቱም በኩል በሚደረጉና በ3ኛው የሜዳ ክፍል ሲደርስ በሚበላሹ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ቀጥሎ በ85ኛው ደቂቃ አንቶኒ ላፎር ሰፊ ክፍተት ከነበረበት የግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ በስታድየሙ ጸጥታን አስፍኗል፡፡

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ሰንዳውንስ ሁለት የተከላካይ መስመር ተጫዋቾችን ቀይሮ በማስገባት መሪነቱን ማስጠበቅ ሲችል ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ጨዋታው በእንግዳው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው ከ13 አመታት በኋላ (ከ15 ጨዋታ በኋላ) በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የመጀመርያ ሽንፈቱን ሲያስተናግድ ወደ ሩብ ፍጻሜ የማለፍ ተስፋውም ጨልሟል፡፡ በሌላ የምድቡ ጨዋታ ኤስፔራንስ ከ ቪታ አቻ በመለያየቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጨረሻ ጨዋታውን ቢሸንፍ እንኳን ወደ ሩብ ፍጻሜ እንደማያልፍ አረጋግጧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *