” በጣም ጠንካራ ሰራተኛ ከሆኑ ሰዎች አንዱ ነኝ” አብዱልከሪም ኒኪማ

በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ እየተወዳደረ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ቱኒዚያ በመጓዝ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን በመጪው እሁድ ከኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ጋር ያደርጋል፡፡ በዘንድሮው የፕሪምየር ሊጉም ሆነ በቻምፒየንስ ሊጉ የቡድኑ ጉዞ ጉልህ አስተዋጽኦ ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የዘንድሮ ፈራሚ የሆነውና በመጀመሪያ ዓመቱ የቡድን አጋሮቹንም ሆነ የደጋፊዎቹን ልብ ለማሸነፍ የቻለው ቡርኪናፋሷዊው አብዱልከሪም ኒኪማ ዞኮ ነው፡፡ የሶከር ኢትዮጵያ ተባባሪ አዘጋጅ ተሾመ ፋንታሁን አብዱልከሪም ወደ ቱኒዚያ ከማቅናቱ በፊት ቦሌ በሚገኘው የክለቡ የመለማመጃ ስፍራ ተገኝቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ በቻምፒየንስ ሊግ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ አነጋግሮታል፡፡

የመጀመሪያ ዓመት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታህን እንዴት ትገልጸዋለህ ?

የመጀመሪያ ዓመት ቆይታዬ መጥፎ የሚባል አይደለም፡፡ የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ሆነናል፡፡ በጣም ደስ የሚል ጊዜ፣ እጅግ ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ በግልም የተማርኩበት ጊዜ ነው፡፡ ከፍተኛ ልምድ አግኝቼበታለው፡፡

በቡድን የፕሪምየር ሊጉ ቻምፒዮን ፣ በቻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ የምድብ ድልድል ውስጥ ገብታችኋል፡፡ በግል ደግሞ በሁሉም ጨዋታዎች ቋሚ ተሰላፊ ከመሆን ባሻገር ለክለቡ ወሳኝ ተጫዋች መሆንህን በአንድ ዓመት አስመስክረሃል. . .

ምክንያቱ ጠንካራ ሰራተኛ መሆኔ ነው፡፡ እዚ ያመጣኝ እግር ኳስ ነው፡፡ እግርኳስ ሜዳ ከገባው ኳስን ብቻ ነው የማስበው፡፡ በጣም ጠንካራ ሰራተኛ ከሆኑ ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ ይህ ብቻ ግን አይደለም፣ የቡድኔን አሰልጣኞችና ተጫዋቾችም ምስጋና ይገባቸዋል፤ በደስታ ተቀብለው በቀላሉ እንድላመድ ነገሮችን ቀላል አድርገውልኛል፡፡

በቻምፒየንስ ሊጉ ጉዟችሁን እንዴት ታየዋለህ?

መጀመሪያ ላይ በጣም ከባድ ነበር፡፡ ከዛ ግን እኛም በጣም እየተሻሻልን መጣን ፤ በተለይ 16 ውስጥ ከገባን በኋላ ሁላችንም የቻልነውን ሁሉ ለማድረግ ለራሳችን ቃል ገባን፡፡ በጣም ጥሩ ደረጃም ነው የደረስነው፣ በአጠቃላይ የዘንድሮ አካሄዳችን በጣም ጥሩ ነበር፡፡ በፍጹም ልናዝን አይገባም ፤ ምክንያቱም እዚህ ደረጃ ስንደርስ የመጀመሪያችን ነው፡፡ ብዙ ልምድ አግኝተንበታል፣ ትምሕርት ተምረንበታል፣ በሚመጡት ዓመታት ይህን ልምድ ተጠቅመን ከዚ የተሻለ መሄድ እንችላለን፡፡ በሃገሪቱ ያሉ ክለቦችም ጊዮርጊስን እንደአርኣያ መውሰድ ይችላሉ፡፡

ከምድቡ መሰናበታችሁን ያረጋገጣችሁበትን (ከሰንዳውንስ ጋር አዲስ አበባ ላይ የነበረውን) ጨዋታ እንዴት አገኘኸው?

ልናሸንፍ የምንችለውና ማሸነፍ የነበረብን ጨዋታ ነበር ፤ በእግር ኳስ የማይሆን ነገር የለም፡፡ ያለንን ሁሉ ሳንሰስት ሰጥተናል፣ የምንችለውን ሁሉ አድርገናል፡፡ ነገር ግን እድል ከኛ ጋር አልነበረችም፡፡

ጊዮርጊስ በመጀሪያው ግማሽ አሸንፎ ሊወጣ የሚችልበት አጋጣሚዎች ፈጥሮ ነበር፡፡ ምንድነው ልክ ያልነበረው?

የማንም ስህተት አይደለም፣ እግር ኳስ እንደዚ ነው፣ እስከመጨረሻው ድረስ የምንችለውን ሁሉ አድርገናል፡፡ በርግጥ በመጀመሪያው ግማሽ ሁለት ሶስት ኳሶችን ማግባት እንችል ነበር፤ አልሆነም እድል ከኛ ጋር አልነበረችም፡፡ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጎል ተቆጥሮብን ተሸንፈናል፡፡

ብዙ ተመልካቾች በተለይ ከተጫዋች ቅያሪ ጋር በተያያዘ የአሰልጣኝ ስህተት ነበር ይላሉ (የበኃይሉና የፕሪንስ ቅያሪ) አንተስ ምን ትላለህ?

እኔ የቅያሪ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ እኔም በክንፍ ስጫወት የመጀመሪያዬ አይደለም፤ እኔ ብቻ ሳልሆን ሁላችንም እየተቀያየርን እንጫወታለን የመሃል ሜዳ ተጫዋች ብሆንም ወደክንፍ እየወጣሁ እጫወታለው፡፡ ስለዚህ የቅያሪ ጉዳይ አይመስለኝም ነገር ግን እድለኛ አልነበርንም፡፡

ለጊዮርጊስ በመጫወትህ የሚሰማህን ስሜት ግለፅልኝ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ብዙ ደጋፊዎች ያሉት በጣም ትልቅ ክለብ ነው፡፡ የክለቡ ሃላፊዎችና ደጋፊዎች ክለቡን መደገፋቸውን ከቀጠሉ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ጊዮርጊስ ከአፍሪካ አራት ወይም ስምንት ትላልቅ ክለቦች አንዱ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡

ከክለብ ጓደኞችህ ጋር ያለህስ ግንኙነት፤ ቋንቋ፣ ምግብ፣ ባህል አላስቸገረህም?

እኔን ብዙ አላስቸገረኝም፡፡ ምክንያቱም የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኞ የሆነው ንዲዝዬ ኤሚ ፈረንሳይኛ ይናገራል፡፡ እኔም ብሆን እንግሊዝኛ እናገራለው ፤ ስለዚህ ብዙ አልተቸገርኩም፡፡ ምግቡም ቢሆን በጣም ተመችቶኛል እንጀራም እመገባለው፡፡ እንጀራ በጣም እወዳለው፣ እንጀራ በጥብስ እመገባለው፡፡

በክለቡ የቅርብ ጓደኛህ ማነው ?

ናትናኤል ዘለቀ ነው፡፡ ብዙ ጊዜዬን ከናትናኤል ጋር ነው የማሳልፈው፡፡ እንግሊዝኛ ይናገራል ጥሩ ወዳጄ ነው፡፡

የሚመጣው ዓመት እቅድህስ ምንድን ነው?

አሁን ሁሉም ነገር እየተጠናቀቀ ነው፡፡ የመጨረሻ ጨዋታችንን በቱኒዝ እናደርጋለን ከዛም ስንመለስ ወደ ቤተሰቦቼ እሄዳለው፡፡ እዛም እረፍት እያደረግኩ ለመጪው ዓመት በደንብ አስባለው፡፡

ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ትመለሳለህ?

ፈጣሪ ነው የሚያውቀው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *