ወላይታ ድቻ – የ2009 የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ አሸናፊ !

የ2009 የኢትዮጵያ ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) የፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በመከላከያ እና ወላይታ ድቻ መካከል ተደርጎ ወላይታ ድቻ በመለያ ምቶች 4-2 በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡

በጨዋታ መደራረብ እና ዝናብ ምክንያት ለጨዋታ ምቹ ባልሆነው አዲስ አበባ ስታድየም የተጫወቱት ሁለቱ ክለቦች ዋንጫውን ከማንሳትም በላይ በቀጣይ አመት (2018) የካፍ ቶታል ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ብርቱ ፉክክር አድርገው ነበር።

በመጀመሪያው አጋማሽ የተቀዛቀዘ የጨዋታ እንቅስቃሴ የነበረ ሲሆን በደጋፊቻቸው የታጀቡት ወላይታ ድቻዎች በተሻለ ፍጥነት ወደ ግብ ለመድረስ ሙከራዎች አድርገዋል፡፡ ሆኖም ከሜዳው አለመመቸት አንፃር ሁለቱም ቡድኖች ረጃጅም ኳሶችን ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል።

በ21ኛው ደቂቃ ከባዬ ገዛኸኝ በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ሳሙኤል ሳሊሶ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ወደ ግብ ለመምታት ሲሞክር ሙባረክ ሽኩር ቀድሞ ለማውጣት በመንካቱ አቅጣጫ ውን ቀይሮ በራሱ መረብ ላይ በማስቆጠር መከላከያዎችን መሪ አድርጓል።

ከጎሉ መቆጠር በኃላ በእንቅስቃሴ እየወረዱ የመጡት መከላከያዎች መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ተረጋግተው በራሳቸው ሜዳ ላይ ሲጫወቱ ተስተውሏል። ወላይታ ዲቻዎች በበኩላቸው በአላዛር ፋሲካ እና በበዛብህ መለዮ አማካኝነት ጎል ለማስቆጠር በተናጠል ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው የመጀመሪያው አጋማሽ በመከላከያ 1-0 መሪነት ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ የተሻለ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በተደጋጋሚ የመከላከያን የግብ ክልል በመፈተሽ ጫና መፍጠር ችለዋል፡፡ ጫናቸውም ፍሬ አፍርቶ በ53ኛው ደቂቃ ይድነቃቸው ኪዳኔ በጨዋታው አስደናቂ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው የመስመር ተከላካዩ አናጋው ባደግ ላይ በሰራው ጥፋት የፍጹም ቅጣት ምት እግኝተዋል፡፡ የፍጹም ቅጣት ምቱንም አላዛር ፋሲካ በጥሩ ሁኔታ መትቶ በማስቆጠር አቻ መሆን ችለዋል፡፡

ወላይታ ድቻዎች ከጎሉ መቆጠር በኃላም ተጨማሪ ግበብ ለማግኘት ጫና መፍጠራቸውን ቀጥለው እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማደድረግ ችለዋል፡፡ በተለይም በ63ኛው እና በ66ኛው ደቂቃ ከፈቱዲን ጀማል የተሻገሩትን ግልጽ የጎል ማስቆጠር እድሎች በዛብህ መለዮ እና አላዛር ፋሲካ አምክነዋቸዋል፡፡ የጨዋታው መደበኛ ክፍለጊዜም 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

አሸናፊውን ለመለየት የመለያ ምቶች የተሰጡ ሲሆን በመከላከያ በኩል ባዬ ገዛኸኝ እና ሳሙኤል ሳሊሶ የመለያ ምቱን ሲያስቆጥሩ አወል አብደላ እና ግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔ ማስቆጠር አልቻሉም። በወላይታ ድቻ በኩል ተክሉ ታፈሰ አላዛር ፣ ፋሲካ አብዱልሰመድ አሊ እና ግብ ጠባቂው ወንድወሰን ገረመው ሲያስቆጥሩ ፈቱዲን ጀማል የመታው ደግሞ በይድነቃቸው ተመልሶበታል። ወላይታ ድቻም 4-2 በማሸነፍ የ2009 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል፡፡

ወላይታ ድቻዎች የውድድሩን ዋንጫ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የተቀበሉ ሲሆን ከደጋፊዎቻቸው ጋር በከፍተኛ ስሜት ድላቸውን አጣጥመዋል፡፡

በሰኔ ወር 2001 የተመሰረተው ወላይታ ድቻ 8ኛ አመቱን ባከበረበት ወር በታሪኩ የመጀመርያውን ዋና ክብር (Major Title) ማሳካት ችሏል፡፡ በ2018 ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ መካፈሉን በማረጋገጡም ከ10 አመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገኝ ክለብ በአፍሪካ ውደድድር የሚሳተፍም ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *