ኮንፌድሬሽን ዋንጫ፡ የወቅቱ ቻምፒዮን ማዜምቤ እና ሱፐርስፖርት ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል

በቶታል ካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የ2016 አሸናፊው ቲፒ ማዜምቤ ከምድብ አራት በመሪነት ወደ ሩብ ፍፃሜ ሲያልፍ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ ሞናና ላይ 4 ግብ አስቆጥሮ በሁለተኝነት ማለፉን አረጋግጧል፡፡ በምድቡ ሁለት አስቀድመው ማለፋቸውን ያረጋገጡት ሴፋክሲየን እና ኤምሲ አልጀር በተገናኙበት ጨዋታ የቱኒዚያው ክለብ 4-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ሲችል ፕላቲኒየም ስታርስ ከምባባን ስዋሎስ 2 አቻ ተለያይተዋል፡፡

ሉቡምባሺ ላይ ቲፒ ማዜምቤ በጥብቅ መከላከል አጨዋወት ከረጅም ደቂቃ ሃያል የነበረውን ሆሮያ 2-1 በማሸነፍ የአምና ስኬቱን ለመድገም ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ የዲዮ ካንዳ ግብ ማዜምቤን መሪ ብታደርግም ፍራንሲስ ዲፒታ ያስቆጠራት የአቻነት ግብ ሆሮያን ወደ ቀጣዩ ዙር እንዲያልፍ የሚስችል ነበር፡፡ ሆኖም በሁለተኛው አጋማሽ የኮናክሬው ክለብ የመረጠው የመከላከል ስትራቴጂ ስኬታማ ያደረገው እስከ82ኛው ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ ዛምቢያዊው ኢንተርናሽናል ናታን ሲንካላ አክርሮ የመታው ኳስ የጊኒው ክለብ መረብ ላይ አርፋ ቲፒ ማዜምቤን ወደ ቀጣዩ ዙር አሻግራለች፡፡

ፕሪቶሪያ ላይ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ የጋቦኑን ሞናናን 4-1 በማሸነፍ ከምድብ አራት ያለፈ ሁለተኛው ክለብ ሆኗል፡፡ የደቡብ አፍሪካው ክለብ በመጀመሪያው 45 ያስቆጠራቸው 4 ግቦች 4-0 እንዲመራ እና ጨዋታውን በቀላሉ እንዲያሸንፍ አድርጎታል፡፡ ብራድሊ ጎሎብለር፣ ታቦ ምናያማኔ፣ ጀርሚ ብሮኪ (ሁለት) የግቦቹ ባለቤቶች ናቸው፡፡ የሞናናን ማስተዛዘኛ ግብ ኤሊሳ ሜንሳ በሁለተኛው አጋማሽ ከመረብ አዋህዷል፡፡

ምድቡን ቲፒ ማዜምቤ በ12 ነጥብ ቀዳሚ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ በ10 ነጥብ ሁለተኛ ሆኗል፡፡ ሆሮያ በ9 እንዲሁም ሁሉንም ጨዋታ የተረታው ሞናና ያለምንም ነጥብ ተከታዮቹን ደረጃዎች በመያዝ ጨዋታቸውን አጠናቅቀዋል፡፡

የምድብ ሁለት የበላይነት ለመያዝ በተደገረው ጨዋታ ሴፋክሲየን በፊራስ ቻዎት (ሁለት)፣ ኦሳማ አምዱኒ፣ አላ ማርዙኩ ግቦች ኤምሲ አልጀርን 4-0 ረቷል፡፡ በጨዋታው ላይ የቱኒዚያው ክለቦች ያስቆጠራቸውን ሶስት ግቦች የተገኙት ከ88ኛው ደቂቃ በኃላ መሆኑ የኤምሲ አልጀር የተከላካይ መስመር ብቃት ላይ ጥያቄ አስነስቷል፡፡

ደቡብ አፍሪካ ላይ ፕላቲኒየም ስታርስ ከመመራት ተነስቶ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ከስዋዚላንሱ ምባባን ስዋሎስ ጋር 2-2 ተለያይቷል፡፡ ዋንደር ንሌኮ እና ልማደኛው ሳቤሌ ንድዚኒሳ የስዋዚላንዱን ቻምፒዮን 2-0 መሪ ቢያደርጉም የማላዊው ሮበርት ንጋምቢ የ80 እና 87ኛ ደቂቃ ሁለት ግቦች ፕላቲኒየም ስታርስን ከመሸነፍ ታድገዋል፡፡

ምድብ ሁለትን ሴፋክሲየን በ13 ነጥብ አንደኛ ሲሆን ኤምሲ አልጀር በ11 ነጥብ ሁለተኛ ሆኗል፡፡ ምባባን ስዋሎስ በ5 እንዲሁም አንድም ጨዋታ ያላሸነፈው ፕላቲኒየም ስታርስ በ3 ነጥብ ሶስተኛ እና አራተኛ በመሆን ውድድራቸውን ጨርሰዋል፡፡

አንጎላ ላይ ሬክሬቲቮ ሊቦሎ ከስሞሃ ጨዋታቸውን ያለግብ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ሊቦሎ ሩብ ፍፃሜውን ከምድብ ሶስት ተቀላቅሏል፡፡

ወደ ሩብ ፍፃሜ ያለፉ ክለቦች

ክለብ አፍሪካ (ቱኒዚያ)፣  ክለብ ስፖርቲፍ ሴፋክሲየን (ቱኒዚያ)፣ ፋት ዩኒየን ስፖርት (ሞሮኮ)፣ ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ)፣  ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ)፣ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ (ደቡብ አፍሪካ) ክለብ ሬክሬቲቮ ዴስፖርቲቮ ዱ ሊቦሎ (አንጎላ) እና ሞውሊዲያ ክለብ ደ አልጀር (አልጄሪያ)

 

የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች

ክለብ አፍሪካ ከ ሞውሊዲያ ክለብ ደ አልጀር

ክለብ ስፖርቲፍ ሴፋክሲየን ከ ፋት ዩኒየን ስፖርት

ቲፒ ማዜምቤ ከ ክለብ ሬክሬቲቮ ዴስፖርቲቮ ዱ ሊቦሎ

ሱፐርስፖርት ዩናይትድ ከ ዜስኮ ዩናይትድ

 

የአርብ ውጤቶች

ክለብ አፍሪካ 4-0 ካምፓላ ሲቲ ካውንስል ኦቶሪቲ

ፋት ዩኒየን ስፖርት 2-1 ሪቨርስ ዩናይትድ

 

የቅዳሜ ውጤቶች

ቲፒ ማዜምቤ 2-1 ሆሮያ አትሌቲክ ክለብ

ሱፐርስፖርት ዩናይትድ 4-1 ሲኤፍ ሞናና

ክለብ ስፖርቲፍ ሴፋክሲየን 4-0 ሞውሊዲያ ክለብ ደ አልጀር

ፕላቲኒየም ስታርስ 2-2 ምባባን ስዋሎስ

 

የእሁድ ጨዋታ

ክለብ ሬክሬቲቮ ዴስፖርቲቮ ዱ ሊቦሎ 0-0 ስሞሃ

ዜስኮ ዩናይትድ ከአል ሂላል ኦባያድ የሚያደርጉት ጨዋታ የሱዳን እግርኳስ ማህበር በፊፋ በመታገዱ አይደረግም፡፡ ዜስኮ በፎርፎ አሸናፊ ሆኗል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *