አዲስ አበባ ከተማ በፍጥነት ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመመለስ አልሟል

የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በአዳማ ከተማ የጀመረው የአአ ከተማ እግርኳስ ክለብ በሜዳም ሆነ ከሜዳም ውጭ ዝግጅቱን አስቀድሞ በመጀመር አጠናክሮ ቀጥሏል።

ከተመሰረተ ስድስተኛ አመቱን ጨርሶ ወደ ሰባተኛ አመቱ የተሻገረው የአአ ከተማ እግር ኳስ ክለብ በአምስት አመት ውስጥ የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ የመቀላቀል እቅዱን በ2009 አመት አሳክቶ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ መሳተፍ ችሏል። በፕሪምየር ሊጉ በነበረው ቆይታ አጀማመሩ ጥሩ የነበረ ቢሆንም የኋላ ኋላ ከተለያዩ ውጫዊ ችግሮች በመነሳት በመጣበት አመት የደረጃ ግርጌውን በመያዝ ወደ ከፍተኛ ሊግ ተመልሶ ሊወርድ ችሏል ።

አአ ከተማ እግር ኳስ ክለብ በ2009 የፕሪምየር ሊጉ ቆይታው የነበሩበትን ችግሮች በዝርዝር ከገመገመ በኃላ በዋናነት መሰረታዊ ችግሮች ናቸው ያላቸውን ሦስት ነገሮችን ገልጿል፡፡ እነሱም፡-

1ኛ. የቅድመ ውድድር ዝግጅት በበቂ ሁኔታ አለመሰራት ለቡድኑ ውጤት መውረድ ምክንያት ሆኗል።

2ኛ. የተጨዋቾች አመላመል ፣ ግዢ ፣ የተጨዋቾች የጤንነት ሁኔታን ምንም አይነት የህክምና ምርመራ ሳይደረግ ወደ ቡድኑ በከፍተኛ ሂሳብ እንዲቀላቀሉ ማድረጉ፡፡

3ኛ. አመራሩ በተጠናከረ ሁኔታ ተናቦ ከክለቡ አባላት ጋር በጋራ አለመስራት ለመውረዱ መሰረታዊ ችግሮች እንደነበሩ አሳውቋል።

ከዚህ ድክመቶቹ በመነሳት በ2010 ለሚኖረው የከፍተኛ ሊግ ቆይታ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ በማድረግ በ2011 ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲመለስ ለማስቻል በአዳማ ከተማ ኮንፈርት ሆቴል ማረፊያውን በማድረግ በቀን ሁለቴ የሜዳ ላይ ተግባር ልምምድ እያደረገ ከመሆኑ ባሻገር ያለፉትን ሦስት ቀናት የተለዩ ስልጠናዎችን ወስደዋል። ሐሙስ በነበረው ፕሮግራም የአሸናፊነት መንፈስን ለመላበስ ይረዳ ዘንድ በባለሙያ የታገዘ የስነ ልቦና ትምህርት ሲሰጥ አርብ በነበረው ፕሮግራም የክለቡን አጠቃላይ የዲስፒሊን መመሪያ ተጨዋቾቹ በሚገባ እንዲያውቁ በማሰብ በክለቡ ሀላፊዎች ማብራርያ ተሰቷቸዋል።

ቅዳሜ በነበረው ፕሮግራም ከቀኑ 08:00 ጀምሮ በአዳማ ኮንፈርት አዳራሽ የክለቡ የቦርድ አመራሮች የሆኑት ዶ/ር ታቦር ገ/መድን ፣ የተከበሩ አቶ ካሚል አህመድ እና ሌሎች የቦርድ አባላት ፣ የክለቡ ተወካዮች ፣ የቡድኑ አጠቃላይ አባላል በተገኙበት የክለቡን ቀጣይ ጉዞን በተመለከተ ውይይት እና የትውውቅ መርሀግብር ተካሂዷል።

የዕለቱ የክብር እንግዶች የሆኑት የክለቡ የቦርድ አመራሮች ከተጨዋቾቹ ጋር ትውውቅ ካደረጉ በኋላ ፣ ባደረጉት ንግግር አአ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረደው በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ከሚሳተፉ ሌሎቹ ክለቦች በአቅም ፣ በአደረጃጀት አንሶት ወይም በጨዋታ ብልጫ ተወስዶበት ሳይሆን የተለያዩ የአሰራር ችግሮች ክለቡን ለመውረድ እንዳበቁት ተናግረዋል። ዘንድሮ ከስህተቱ ተምሮ ከተጨዋቾች ምልመላ ፣ ከጤና ምርመራ አንስቶ ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል ብለዋል። በቀጣይ ክለቡ በከፍተኛ ሊግ ውድድር በሚኖረው ተሳትፎ የክለቡ የቦርድ አመራር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቀው የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ተናግረው ከውጤቱ ባሻገር አስተዳደሩና ህዝቡን የሚመጥን ጠንካራ ቡድን እንዲሆን እንደሚፈልጉ ገልፀዋል። አስተዳደሩ አስቀድሞ ዝግጅቱ እንዲጀመር ያደረገው ምንያህል ለቀጣይ አመት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ቡድኑ እንዲመለስ ለማድረግ ያለውን ተነሳሽነት ያሳያል ሲሉም አክለዋል። በመጨረሻም አሰልጣኞቹ እና ተጨዋቾቹ የክለቡ የቦርድ አመራር ለክለቡ የሰጡት ትኩረት ከፍተኛ እንደሆነ ዛሬ እዚህ መገኘታቸው አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልፀው ‘እናተም ከእኛ ጎን ከሆናቹ ድጋፋቹሁም የማይለን ከሆነ እኛ በምንችለው ሁሉ ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲመለስ የቻልነውን ሁሉ ለማድረግ ቃል እንገባለን’ ብለዋል። በመቀጠል አስፈላጊ ነው ባሉት ጉዳዮች ዙርያ ጥያቄ አቅርበው ከመድረኩ ምላሽ በመስጠት መርሀ ግብሩ ተጠናቋል፡፡

አአ ከተማ በርከት ያሉ ኮንትራታቸው ያላለቀ ነባር ተጨዋቾች እንዳሉ ሆኖ ከተለያዩ ክለቦች 12 ተጨዋቾችን በዝውውር እና በውሰት ያስፈረመ ሲሆን ከታዳጊ ቡድኑ ተጨማሪ ተጨዋቾችን አሳድጓል። በቅርቡም ከሀገር ውስጥ አልያም ከውጭ አንድ ግብ ጠባቂ ሊያስፈርም እንደሚችል ታውቋል።

አአ ከተማ እግር ኳስ ክለብ የከፍተኛ ሊግ ተሳታፊው የወንዶች ቡድኑ ፣ በኢትዮዽያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚካፈለው የሴቶች ቡድኑ ፣ በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ከ17 አመት በታች ውድድር ላይ ካለው ታዳጊ ቡድኑ በተጨማሪ በኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ ከ20 አመት በታች ውድድር ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ሊወዳደር ቅድመ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ለማወቅ ችለናል ። ይህ እውን የሚሆን ከሆነ አቅሙ እያላቸው ከ20 አመት በታች ቡድን ላላቋቋሙ ክለቦች ትልቅ አብነትና ምሳሌ ያለው ተግባር ነው ማለት ይቻላል።

በመጨረሻም በቀጣይ ቀናቶች የክለቦቻችንን ቅድመ ዝግጅት እንቅስቃሴ ሰፋ ባለ ሁኔታ በተከታታይ ይዘን የምንመለስ መሆኑን ከወዲሁ እንገልፃለን ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *