​የአስኮ ፕሮጀክት ቅኝት – ክፍል ሁለት

የአስኮ ፕሮጀክትን በክፍል አንድ ስለ አጠቃላይ አደረጃጀቱ እና ገፅታው ምን እንደሚመስል አስቃኝተናቹ ነበር። በዛሬው መሰናዷችን የፕሮጀክቱ መስራች ከሆነው አብይ እንዲሁም በፕሮጀክቱ በመሰልጠን ላይ ከሚገኙ ታዳጊዎች ጋር የነበረንን ቆይታ በተጨማሪም ፕሮጀክቱ በቀጣይ ከዚህ በተሻለ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሊደረግለት ስለሚገባ እገዛ እንደሚከተለው አቀረብን፡፡

እግር ኳስን ተጨዋች የመሆን  ፍላጎቱ በጉዳት በተለያዩ ምክንያቶች መጨናገፉ እና በአካባቢው ያሉት ወጣቶች በክለብ ፣  በብሔራዊ ቡድን የመጫወት ዕድል ያላገኙ ተጨዋቾች መኖራቸው ቁጭት ፈጥሮበት ፕሮጀክቱን ለመክፈት እንዳነሳሳው የሚናገረው የፕሮጀክቱ መስራች አብይ በፕሮጀክቱ የ16 አመት ቆይታ  ታዳጊዎችን በማሰልጠን በስነ ምግባር የታነፁ ብቁ ዜጋ አድርጎ ማፍራቱ ፣ ዛሬ ለክለብ እና ብሔራዊ ቡድን የሚጫወቱ እግር ኳስ ተጨዋቾችን ከፕሮጀክቱ ወጥተው ሲጫወቱ ማየቱ በጣም ደስተኛ እንዳደረገው ይገልጻል። አሁን ፕሮጀክቱ የደረሰበት ስኬት ለመድረስ በርካታ ስራዎች የተሰሩ መሆኑን የሚናገረው አብይ በቀጣይ አመት ከመቼውም በተሻለ ሁኔታ የፕሮጀክቱን እንቅስቃሴ ለማጠናከር አቅደው እየሰሩ መሆኑን በተለይ ፕሮጀክቱ ቋሚ የሆነ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው  እቅዶች በዝርዝር እንዳወጡ ተናግሯል፡፡

” በመጀመርያ በርካታ ታዳጊዎችን በማሰልጠን ዛሬ በሊጉ ከፍተኛ ተከፋይ ማድረጋችን ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ከእነሱ አልፈው ቤተሰባቸውን መርዳት እንዲችሉ ተጠቃሚ አድርገናል፡፡ በዚህ ረገድ መንግስት ከወጣቶች ጋር ተያይዞ ካስቀመጠው አቅጣጫ አንፃር ፕሮጀክቱ እያበረከተው ያለው አስተዋፆኦ ከፍተኛ በመሆኑ ሊደግፈን ሊያግዘን ይገባል በማለት እየተንቀሳቀስን ነው። በሌላ በኩል የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ታዳጊዎች በፕሮጀክት ታቅፈው መሰልጠን እንዲችሉ የተቀመጠውን ህግ ተግባራዊ ማድረግ አለበት፡፡ በሌላ መልኩ ክለቦች ከታች ወደ ዋናው ቡድን ሲያሳድጉ ለሦስት አመት በነፃ እንዲያገለግሉ ህግ  ይፈቅድላቸዋል፡፡ ሆኖም  ተጨዋቾቹ ወደ ሌላ ክለብ መሄድ ቢፈልጉ ግን ለክለቡ ገንዘብ ከፍለው ነው የሚሄዱት፡፡ ይህ አሰራር ደግሞ ልጆቹን የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶችን ተጠቃሚ አያደርግም። ስለዚህ ተጨዋቹን  ክለብ ሲወስዳቸው ክለቦች ለፕሮጀክቱ ድጋፍ ማድረግ የሚያስገድድ ህግ ሊወጣለት ይገባል። ሌላው በፕሮጀክቱ እየሰለጠኑ የሚገኙ ታዳጊዎች ከውጭ ሀገር ከሚገኙ ኤጀንቶች ጋር በመነጋገር ወደ ውጭ ሀገራት ክለቦች በሽያጭ የሚሄዱበትን አሰራር እየቀየስን እንገኛለን፡፡ ” በማለት የሚናገረው አብይ ከዚህ ባሻገር በተመጣጣኝ ዋጋ አቅሙ ያላቸውን ቤተሰቦች በማናገር ከፍለው በፕሮጀክቱ ታቅፈው እንዲሰለጥኑ የሚያደርግ ስራ ለመስራት እንዳሰቡ ገልጿል፡፡

” በአጠቃላይ በ2010 አመት በርካታ ስራዎችን እንሰራለን ብለን አቅደን እየተንቀሳቀስን ሲሆን እስካሁን ላለንበት ስኬት ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉልን ድርጅቶች እና ባላሀብቶች በተለይ ፕሮጀክቱ ባለበት አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች ለሚያደርጉልን ከፍተኛ ድጋፍ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን። ”
ሶከር ኢትዮዽያ በፕሮጀክቱ የስልጠና መርሀ ግብር ወቅት ከተመለከተቻቸው ታዳጊዎች መካከል በጣም አስገራሚ ክህሎታቸውን ሲያሳዩ ከነበሩ ተስፈኛ ታዳጊዎች ከሆኑት ጋር የተወሰነ አጭር ቆይታ ባደረግንበት ወቅት አሁን ከፕሮጀክቱ የተሰጠውን የአምስት አመት ስልጠና አጠናቀው ወደ ክለብ የሚሄዱበት ጊዜ እንደሆነ ተናግረዋል። በፕሮጀክቱ በነበራቸው ቆይታ ሳይንሳዊ የሆነ ጠቃሚ ስልጠና እንዳገኙ ተናግረው ወደፊት በሚኖረው የእግር ኳስ ህይወታቸው ከዚህ ቀደም በፕሮጀክቱ ሰልጥነው ትላልቅ ክለቦች ፣ በብሔራዊ ቡድን መጫወት እንደቻሉት ተጨዋቾች መሆን እንደሚፈልጉ እና ለእዚህም ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።


እንዳጋጣሚ ሆኖ በታዳጊዎቹ ስልጠና ወቅት መልማዮችን በመላክ ሲከታተሉ የነበሩ የኢትዮዽያ ቡና እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ የክለብ ተወካዮች የፕሮጀክቱ በርካታ ሰልጣኞችን ለቀጣይ ከአስራ ሰባት አመት በታች ቡድናቸው እንደወሰዷቸው ለማወቅ ችለናል። በዚህ ጉዳይ ያናገርነው የፕሮጀክቱ አሰልጣኝ የሆነው ደስታ ታዳጊዎቹ በፕሮጀክቱ በነበራቸው ቆይታ ጥሩ የስልጠና ጊዜ ማሳለፋቸውና በሄዱበት ሁሉ መልካም የእግርኳስ ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝቶ በሄዱበት ክለብ ስለሚኖራቸው ቆይታ ግን ስጋቱን አስቀምጧል፡፡ ” በአስኮ ፕሮጀክት በነበራቸው የአምስት አመት ቆይታ ያገኙትን ሳይንሳዊ ስልጠና ወደ ክለብ ካመሩ በኋላ ክለቦች የሚከተሉት የስልጠና መንገድ የተዘበራረቀ መሆኑ ብዙ ጊዜ ታዳጊዎች እንዲቸገሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ክለቦች ዘመኑ የሚጠይቀውን ሳይንሳዊ የስልጠና መንገድ ሊከተሉ ይገባል ” ይላል፡፡

ከምስረታው ጀምሮ በርካታ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ከፍተኛ ድጋፍ እንዳደረጉለት የሚነገረው የአስኮ ፕሮጀክት በዋናነት የቀድሞ የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ም/ፕሬዝደንት የነበሩት አቶ ብርሀኑ ትጥቆችን እና የስፖርት መሳሪያዎችን በግል ተነሳሽነት ድጋፍ ሲያደርጉ ለማየት ችለናል፡፡ እንደነዚህ ያሉ ድጋፎች ለፕሮጀክቱ ቀጣይ ህልውና አስፈላጊ በመሆኑ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ እየጠቆምን በተለይ ታዳጊዎችን ከፕሮጀክት እየወሰዱ ክለባቸውን ተጠቃሚ እያደረጉ የሚገኙ ክለቦች የሚገባውን ድጋፍ ማድረግ አለባቸው መልክታችን ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *