ሪፖርት፡ የመጨረሻ ደቂቃ ግቦች የኢትየጵያ የማለፍ እድልን አጣብቂኝ ውስጥ ከተውታል

በ2018 ፈረንሳይ ለምታስተናግደው የአለም ከ20 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ ዛሬ በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታድየም ኬንያን የገጠመችው ኢትዮጵያ 2-2 አቻ ተለያይታለች፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጀመርያው አጋማሽ ይዞት የነበረውን የ2-0 መሪነት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠሩበት ግቦች አሳልፎ ሰጥቷል፡፡

በጨዋታው በስታድየሙ ከሚጠበቀው በታች ተመልካች የገባ ሲሆን በጨዋታው የመጀመሪያ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኳስን ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ለመቅረብ ሲሞክሩ የኬንያ ብሔራዊ ቡድን በአንፃሩ ረጃጅም ኳሶችን ወደ ግብ በመሞከር እና የአየር ላይ ኳሶች በመግጨት ለኢትዮጵያ ፈተና ሆኖ ታይቷል፡፡

በጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፈጣን እና ማራኪ እንቅስቃሴን ቢያደርግም በቀላሉ የኬንያን የተከላካይ መስመር ሰብሮ መግባት ሲሳነው ተመልክተናል፡፡ እንደውም አስደንጋጭ የግብ እድል በመፍጠር ረገድ ኬንያዎች ቀዳሚ ነበሩ፡፡ በ8ኛው ደቂቃ ማርታ አውቶሊቲ የሞከረችውና አረጋሽ ፀጋዬ ተንሸራታ ያስጣለቻት ኳስ ኬንያዎችን ቀዳሚ የምታደርግ አጋጣሚ ነበረች፡፡

በባለሜዳው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኩል ምርቃት ፈለቀ እጅግ ግሩም የሆነ አጋጣሚን ከሴናፍ ዋቁማ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል መፍጠር የቻለች ሲሆን አምበሏ የምስራች ላቀውም ከመስመር ወደ ውስጥ በመግባት የግብ እድል ለመፍጠር ስትጥር ታይታለች፡፡ በተለይ በ19ኛው ደቂቃ ቤተልሄም ከፍያለው የወረወረችውን የእጅ ኳስ ምርቃት ፈለቀ በግንባሯ ገጭታ ወደ ውጪ የወጣው ኳስ ለግብ እጅግ የቀረበ ሙከራ ነበር፡፡

ከምርቃት ሙከራ አንድ ደቂቃ በኋላ በተመሳሳይ ቤተልሄም ከፍያለው በረጅሙ ያሻገረችውን ኳስ ምርቃት ፈለቀ በአግባቡ በመቆጣጠር ሊሊያን አዎርን አልፋ ግብ በማስቆጠር ኢትዮጵያን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡ ከግቡ በኋላ የተነቃቁት ወጣቶቹ ሉሲዎች በ27ኛው ደቂቃ አለምነሽ ገረመው በግምት ከ25 ሜትር ርቀት አክርራ በመምታት ባስቆጠረችው ግሩም ጎል የኢትዮጵያን መሪነት ወደ ሁለት አስፍታለች፡፡

ከግቡ በኃላ ኬንያዎች በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል ለመድረስ ሞክረዋል፡፡ ሆኖም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር የመጀመርያው አጋማሽ በኢትዮጵያ 2-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከመጀመሪያው እጅግ የቀዘቀዘ እንቅስቃሴን ሲያደርግ በአንፃሩ የኬንያ አቻው ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥሮ መጫወት ችሏል፡፡ በ55ኛው ደቂቃ ላይ አለምነሽ ገረመው የግብ ጠባቂዋን ሊሊያን አዎር መውጣት ተመልክታ ከርቀት የመታችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ እንደምንም ያወጣችባት እንዲሁም በሴናፍ ዋቁማ እና ምርቃት ፈለቀ አማካኝነት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ጨዋታው ወደ መገባደጃ ደቂቃዎች ሲቃረብ ኬንያዎች በተደጋጋሚ ረጃጅሙ ወደ ግብ በሚሞክሯቸው ኳሶች ግብ ጠባቂዋ ትዕግስት አበራን ሲፈትኑ ቆይተው በመጨረሻም በ88ኛው ደቂቃ ቅድስት ዘለቀ በሎራዞኒ ቪቪያን ላይ የሰራችውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሷ ሎራዞኒ ቪቪያን አስቆጥራ የግቡን ልዩነት ማጥበብ ችላለች፡፡ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተሰጠው 4 ደቂቃዎች ውስጥ ኬንያዎች ይበልጥ ጫና በመፍጠር የአቻነት ግብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ ራቻአሊ ኦቶሮ ኬንያን አቻ ያደረገች ግብ ከማዕዘን ምት ሲሻማ መሬት ለመሬት መታ ማስቆጠር ችላለች፡፡

ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ በሴቶች እግርኳስ እያበበች ያለችው ኬንያ ከሳምንት በኋላ ማቻኮስ ለምታደርገው ጨዋታ ወሳኝ ውጤትን ይዛ ከሜዳ ወጥታለች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *