​በደቡብ ካስቴል ዋንጫ 3ኛ ቀን ውሎ ሀዋሳ ከተማ ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና ከምድቡ ተሰናባች ሆኗል

ከተጀመረ 3ኛ ቀኑን የያዘው የደቡብ ካስትል ዋንጫ የምድብ ሀ ሁለተኛ ጨዋታዎች  ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ስታድየም (ሰው ሰራሽ ሳር) ሜዳ  ተደርገው ፋሲል ከተማ ከ ወላይታ ድቻ አቻ ሲለያዩ ሀዋሳ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን 2-0 በማሸነፍ የማለፍ ተስፋውን አለምልሟል፡፡ 

ፋሲል ከተማ 1-1 ወላይታ ድቻ

በመጀመሪያ ጨዋታቸው ድል የቀናቸው ሁለቱ ክለቦች ጨዋታቸውን 1-1 አጠናቀዋል፡፡ 12 ቢጫ እና ሁለት ቀይ ካርድን ጨምሮ አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔወች በታየበት በዚህ ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች ካለፈው ጨዋታቸው መጠነኛ የተጫዋቾች ለውጦች አድርገው ገብተዋል፡፡

የድቻን የተከላካይ መስመር በተደጋጋሚ ሰብሮ በመግባት አደጋ ሲፈጥር የነበረው አዲሱ የፋሲል ከተማ አጥቂ ክርስቶፈር አሶም አቢ በ36ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አለሙ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ የግብ ጠባቂው ወንደሰን ገረመውን ስህተት ተጠቅም አፄወዎቹን ቀዳሚ አድርጎ የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቋል፡፡

በ55ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከተማ ተከላካዮች በጃኮ አራፋት ላይ በሰሩት ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ጃኮ አራፋት አስቆጥሮ ዲቻዎችን አቻ አድርጓል፡፡ ፋሲሎች በኤፍሬም አለሙ እና አምሳሉ ጥላሁን ያለቀላቸውን የግብ እድል ሲፈጥሩ ወላይታ ድቻዎች በዳግም በቀለ እና በዛብህ መለዮ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ እድሎችን በመፈጠሩ ረገድ የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ፋሲል ከተማወች በ78ኛው ደቂቃ ላይ ተስፉ ኤልያስ ከድር ካይረዲን ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን ፍፁን ቅጣት ምት ራሱ ከድር ካይረዲን ቢመታም ግብ  ጠባቂው ወንደሰን ገረመው አድኗታል፡፡

በ80ኛ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ፀጋዬ ብርሀኑ የፋሲልን ተከላካይ በቡጢ በመማታቱ በቀጥታ ቀይ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ ብዙም ሳይቆይ የፋሲሉ አዲስ ፈራሚ ሮበርት ሴንቶንጎ ኳስ ለማስጣል ከበዛብህ መለዮ ጋር በሚፋለምበት ወቅት ጥፋት ሰርተሀል በሚል አወዛጋቢ የሆነ ቀይ ካርድ መሰጠቱ ጨዋታው ለ5 ደቂቃ ያህል እንዲቋረጥ ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡


ሀዋሳ ከተማ 2-0 ኢትዮጵያ ቡና 

በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸው በተጋጣሚወቻቸው ሽንፈት ያስተናገዱት ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡናን ያገናኘው ጨዋታ የሀዋሳን የማለፍ እድል ሲያለመልም ቡና ከምድቡ ተሰናባች መሆኑን አረጋግጧል፡፡

በጨዋታው ሀዋሳ ከተማ ከመጀመርያው ጨዋታ የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳየ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና በአንጻሱ ተዳክሞ ታይቷል፡፡ በ23ኛው ደቂቃ ፀጋአብ ዮሴፍ 3 ተጫዋቾችን አልፎ ለዳዊት ፍቃዱ አቀብሎት ዳዊት ሲያሻግር የቡናው ግብ ጠባቂ ጁቤድን ትኩረት ማጣት አይቶ ሳዲቅ ሴቾ የቀድም ክለቡ ላይ ግብ አስቆጥሮ ሀዋሳን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ከጎሉ በኋላም ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች በ40ኛው ደቂቃ ላይ አንጋፋው አማካይ ሙሉአለም ረጋሳ የሰጠውን ኳስ አጥቂው ዳዊት ፍቃዱ በግምት ከ20 ሜትር ርቅት አክርሮ መትቶ የሀዋሳን ግብ ወደ ሁለት ከፍ አድርጎ የመጀመሪያው የጨዋታ ጊዜ ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የተስተዋለ ሲሆን በሁለቱም በኩል ጥቂት የግብ እድሎች ቢፈጠሩም ተጨማረ ግቦች ሳይቆጠሩ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋለ፡፡ በውጤቱ መሰረት ሀዋሳ ከተማ የማለፍ ተስፋውን ሲያለመልም ኢትዮጵያ ቡና በ3 የግብ እዳ እና ያለምንም ነጥብ ከምድቡ የተሰናበተ የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *