‹‹በቅርቡ ወደ ሜዳ እመለሳለው›› ሳላዲን ሰዒድ

ሳላዲን ሰዒድ በ2009 ለክለቡ ስኬታማ የውድድር አመት ትልቁን ሚና ከተወጡ ተጨዋቾች አንዱ ነው፡፡ በተለይ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ በምድብ ድልድል ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ሲገባ በስሙ 7 ጎሎችን በማስቆጠር ከፍተኛ አስተዋፆ ነበረው። ሳላዲን ሰኔ 30 ኮንትራቱ መጠናቀቁን ተከትሎ ስሙ ከተለያዩ የግብፅ ክለቦች ጋር ሲነሳ የቆየ ቢሆንም ለተጨማሪ ሁለት አመታት ለመቆየት መስማማቱ ይታወሳል። ያለፉትን ሁለት ወራት በጉልበቱ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ከሜዳ የራቀው ሳላዲን ስለ ጉዳቱ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ውሉን ያራዘመበትን ምክንያት ለሶከር ኢትዮዽያ ተናግሯል፡፡

የጉዳቱ ሁኔታ

ጉዳቱ ያጋጠመኝ ጉልበቴ ላይ ነው፡፡ ህክምናዬን እዚሁ በሀገር ውስጥ በሚገባ ተከታትያለው፡፡ በቂ እረፍት ስለሚያስፈልገው እረፍት አድርጌበታለው፡፡ አሁን ህመሜ በጥሩ ሁኔታ እየተሻሻለ ነው ፤ በጂም እና በሜዳላይም ልምምድ ጀምሬያለው፡፡ ለኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች እደርሳለው።

በግብፅ ስለ ነበረው ቆይታ

ብዙ የግብፅ ክለቦች ጥሪ አድርገውልኝ ሄጄ መጥቻለው፡፡ በሁሉም ነገር ላይ ከስምምነት መድረስ ቢቻልም ክለቦቹ በካፍ ቻንፒየንስ ሊግ ላይ ተሳታፊ አይደሉም፡፡ ያ ደግሞ የተሻለ የመታየት እድል እንዳታገኝ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በቻምፒየንስ ሊግ ለመጫወት በማሰቤ ተመልሼ ለተጨማሪ አመታት ከጊዮርጊስ ጋር ለመቆየት ተስማምቻለው።

ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የእግርኳስ ህይወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ እዚህ ለእኔ የተሻለ ነገር አለ፡፡ አምና የነበረንን ጠንካራ ጉዞ ዘንድሮም እንደግማለን፡፡ አሁን ከጉዳቴ አገግሜ በቅርቡ ወደ ሜዳ ስመለስ ለክለቡ በምችለው አቅም ሁሉ አገልግሎት የምሰጥ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *