ዋሊድ አታ አል ካሊጅን ለቋል

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መለያ አራት ጨዋታዎች ማድረግ የቻለው ዋሊድ አታ ከሳውዲ አረቢያው የአንደኛ ዲቪዚዮን ክለብ አል ካሊጅ ጋር ተለያይቷል፡፡ የ31 ዓመቱ ተከላካይ ክለቡን ለቆ ወደ ስዊድን መመለሱም ታውቋል፡፡

ዋሊድ አል ካሊጅን በመስከረም ወር የተቀላቀለ ሲሆን በፍጥነት ከክለቡ መለያየቱ አግራሞትን አጭሯል፡፡ ዋሊድ ከሌላኛው የሳውዲ ክለብ ናጅራን ጋር ውሉን በስምምነት በማፍረስ ነበር ወደ አል ካሊጅ ያመራው፡፡ ነገር ግን በችግሮች የተሞላውን የሳውዲ ቆይታው በአጭሩ እንዲቋጭ በማድረግ ወደ ስዊድን መመለሱ ታውቋል፡፡ በአል ካሊጅ አጀማመሩ መልካም የነበረው የቀድሞ የኤአይኬ እና ቢኬ ሃከን ተከላካይ ዋሊድ ለክለቡ በሁለተኛ ሳምንት የሳውዲ አረቢያ አንደኛ ዲቪዚዮን ጨዋታ ጅዳ ክለብ ላይ ግብ ማስቆጠር ችሎ ነበር፡፡

ለአንድ ወራት ብቻ በምስራቁ የሳውዲ አረቢያ ክለብ አል ካሊጅ ቆይታ ያደረገው ዋሊድ በደሞዝ እና ቤተሰብ ምክንያት ክለቡን ለመልቀቅ እንደተገደደ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡ “በሳውዲ ቆይታዬ ደስተኛ አልነበርኩም፡፡ በጣም ብዙ ችግሮች ነበሩ ክለቡ እንድለቅ ያስገደዱኝ፡፡ በስራ ፍቃድ ምክንያትም አሰልቺ የሆነ ቆይታ ነበረኝ ይህም ያለምንም ማቅማማት ክለቡን እንድለቅ ምክንያት ሆኖኛል፡፡ ሌላው ቤተሰቤ በሳውዲ መኖርን አለመምረጡ እና የደሞዝ ችግርም ከክለቡ ጋር የነበረኝን ውል እንዳፈርስ አስገድዶኛል፡፡”

ዋሊድ በክለቡ ቃል የተገባለት ነገሮች አለመሟላታቸውን ከላይ ከዘረዘራው ችግሮች ጋር ተዳምረው በ2017 ብቻ የለቀቃቸውን የክለቦች መጠን ወደ 3 አድርሷል፡፡ የስዊድን ሊግ የውድድር ዘመን ሊጠናቀቅ በመቃረቡ በአዲሱ የውድድር ዘመን ዋሊድ አዲስ ክለብ እንደሚያገኝ ተማምኗል፡፡ “አሁን ላይ ወኪሌ ነው ስለቀጣይ ማረፊያ የሚያውቀው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ለየትኛውም ዝውውር ክፍት ነኝ፡፡ የውድድር ዘመኑ አሁን ላይ እዚህ ወደ መጠናቀቁ ነው ስለዚህም ቀጣይ ማረፊያን የማውቀው ወደፊት ነው፡፡” ሲሉ ዋሊድ ለሶከር ኢትዮጵያ ከስዊድን አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ዋሊድ ቢኬ ሃከን በ2015 ከለቀቀ በኃላ ለቱርኩ ገንሰልበርሊጊ፣ ለስዊድኑ ኦስተርሰንድስ፣ ለኖርዌይ ክለብ ለሆነው ሶግንዳል እና ለሳውዲዎቹ ናጅራን እና አል ካሊጅ ለመጫወት ፊርማውን አኑሮ ነበር፡፡ ከእነዚህ አምስት ክለቦች በአንዱ (ኦስተርሰንድስ) ብቻ የተሳካ ግዜ ያሳለፈ ሲሆን ያለፉትን ሁለት ዓመታት ተከላካዩ በዝውውር ተጠምዶ ቆይቷል፡፡ ዋሊድ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በበርካታ ክለብ መለያዎች በመታየቱ ምክንያት ኢትዮጵያዊው ማርኮ ፖሎ የሚል ተቀፅላ ስም ከተሰጠው የፊት መስመር ተጫዋች ፍቅሩ ተፈራ በመቀጠል በበርካታ የውጪ ክለቦች የተጫወተ ተጫዋች ሆኗል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *