​መከላከያ ከ ወላይታ ድቻ – ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ

የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ነገ ሲጀመር መከላከያ ወላይታ ድቻን አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በ11፡30 ላይ ያስተናግዳል።  በጨዋታው ዙሪያ የሚነሱ ዋና ዋና ጉዳዮችን እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።

በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የሊጉን የመክፈቻ ጨዋታ አድርገው የነበሩት ሁለቱ ክለቦች አንድ አንድ ነጥብ ማሳካት ችለዋል። ሰኞ ዕለት አዲስ አበባ ላይ ደደቢትን የገጠመው ወላይታ ድቻ ያለግብ አቻ ሲለያይ በቀጣዩ ቀን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የተገናኘው መከላከያ በበኩሉ 1-0 ከተመራ በኃላ በቴዎድሮስ ታፈስ ድንቅ የቅጣት ምት ጎል ነጥብ ተጋርቶ መውጣት ችሏል። በመሆኑም ነገ እርስ በእርስ የሚገናኙበት ጨዋታ ለቡድኖቹ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማጣጣም ዕድል የሚሰጥ ይሆናል። ሆኖም አምና በሁለተኛው ዙር በመዲናዋ የተገናኙት ሁለቱ ክለቦች ያለ ግብ መለያየተቻው የሚታወስ ነው።

ከሊጉ ክለቦች ልማድ በተቃራኒ ሁለት ተጨዋቾችን ብቻ በማዘዋወር የውድድር አመቱን የጀመረው መከላከያ የተጨዋቾች አማራጭ እጥረት ይስተዋልበታል። በተለይም የቡድኑ አምበል የነበረው ሚካኤል ደስታ ክለቡን መልቀቁን ተከትሎ የበኃይሉ ግርማን ሚና ወደፊት በማስጠጋት አዲስ ፈራሚውን አማኑኤል ተሾመን በተከላካይ አማካይነት እየተጠቀመ ያለው ቡድኑ የአማካይ ክፍሉ ውህደት ላይ ጥያቄ የሚነሳበት ሆኗል። መከላከያ በሚጠቀመው 4-4-2 ጠንካራ ጎን የነበረው የመስመር ተከላካዮች እና የመስመር አማካዮች ጥምረትም እንደወትሮው አለመሆኑ ከፊት የሚጠቀምባቸው ሁለት አጥቂዎች በቂ የኳስ አቅርቦት ከአማካይ ክፍሉ እንዳያገኙ እና አብዛኛዎቹ የሚያደርጓቸው ሙከራዎች ከሳጥን ውጪ የሚደረጉ እንዲሆኑ ምክንያት ሆኗል። ይህም በተለይ ቡድኑ መሀል ሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫ ከተወሰደበት እና ብዙ የማያጠቁ የመስመር ተከላካዮች ያሉት ቡድን ከገጠመው እንዲቸገር የሚያደርገው ይሆናል። የፊት መስመሩ በንፅፅር የተሻለ ሊባል የሚችለው መከላከያ የያዛቸው የአጥቂዎች ጥምረት ከሚፈጠርለት አናሳ የግብ ዕድል አንፃር በአካላዊ ፍጥነት እና በግል ጥረት የሚገኙ አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ይሞክራል።

የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪው ወላይታ ድቻ ከተጋጣሚው በተለየ በዝውውሩ ላይ በስፋት ከተካፈሉ ቡድኖች መሀከል አንዱ ነው፡፡ ቡድኑ ባደረገው የአሸናፊዎች አሸናፊ የፍፃሜ ጨዋታና የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ እንደተስተዋለው አሰልጣኙ በሶስት ተከላካዮች የሚጀምረው አቀራረባቸው አሁንም አብሯቸው አለ። በተጨማሪም ቡድኑ ሶስት አጥቂዎችን ከፊት የሚጠቀም ሲሆን መሀል ሜዳውን ለተከላካይ ክፍሉ እጅግ በቀረቡ ሁለት አማካዮቹ እና በመስመር ተመላላሾቹ ለመሸፈን ይሞክራል ። በተለይ በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ የተሻለ የማጥቃት ተሳትፎ ያደረጉት የመስመር ተመላላሾች (Wing Backs) ወደኃላ ተስበው ከሶስቱ የመሀል ተከላካዮች ጋር በመሆን ጠንካራ የመከላከል መስመር ለመፍጠር ባይቸገሩም ወደ ማጥቃት በሚደረጉ ሽግግሮች ላይ ግን አሁንም ብዙ መሻሻል ይጠበቅባቸዋል። ኳስ በመሀል ተከላካዮች ከኃላ ተመስርቶ ሲወጣ የሚኖራቸው አቋቋም እና ኳሱ በአማካይ መስመር ተጨዋቾች እግር ከገባ በኃላ ከመስመር አጥቂዎች ጋር የሚኖራቸው መናበብ በሚገባ የተጤነ ባለመሆኑ የማጥቃት ወረዳ ውስጥ ሲገቡ የቁጥር ብልጫ ተወስዶባቸው ጥቃታቸው አቅም እንዲያጣ ሲሆን ይስተዋላል። ቡድኑ የፊት አጥቂው ጃኮ አራፋት ይህን የአማካይ እና የአጥቂ ክፍሉን ግንኙነት ለመፍጠር ወደኃላ ተስቦ ኳስ በሚቀበልበት ወቅት ትቶት በሚመለሰው ቦታ ላይ በመግባት ዕድሎችን መጠቀም ላለመቻሉም ይኸው የመስመር አጥቂዎች እና ተመላላሾች አለመናበብ የራሱ የሆነ ሚና አለው።

በነገው ጨዋታ ሰኞ ዕለት የጌታነህን እና የአቤልን ጥምረት በቁጥር ብልጫ ማቆም የቻለው የድቻ የሶስትዮሽ የተከላካይ ክፍል ከምንይሉ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ጋር የሚፋጠጥ ይሆናል። ይህ የድቻ የተከላካይ ክፍል በተሻጋሪ እና የቆሙ ኳሶች ሲቸገር መታየቱ ደግሞ ለጦሩ አጥቂዎች የተሻለ ዕድል ሊሰጣቸው ይችላል ተብሎም ይጠበቃል። ሌላው መሀል ሜዳ ላይ አጥብበው በሚጫወቱ አማካዮቹ እና ወደፊት ሲሄዱ ይታዩ በነበሩት የመስመር ተከላካዮቹ ሚና የሚታወቀው መከላከያ የመስመር ተመላላሾችን ከሚጠቀመው እና በብዛት ትይዩ ሆነው የሚቆሙ ሁለት አማካዮችን ከያዘው እንዲሁም ከመስመር አጥቂዎቹም ተጨማሪ እገዛ የማግኘት ዕድል ካለው የድቻ የአማካይ ክፍል ጋር የሚያደርገው ፍልሚያ የሚጠበቅ ነው። ከዚህ ጎን ለጎንም ጨዋታው መስመር ተኮር የሆነው የሁለቱ ቡድኖች የግብ ዕድል ፈጠራም የሚፈተሽበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የቡድን ዜናዎች

በመከላከያ በኩል ቴዎድሮስ በቀለ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ወደ ሩዋንዳ በመጓዙ ይህ ጨዋታ የሚያልፈው ይሆናል፡፡ አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ በአንፃሩ ከሩዋንዳው ጉዞ በመቀነሱ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል፡፡ በኤሌክትሪኩ ጨዋታ ጉዳት የደረሰበት ሳሙኤል ታዬ እና በጉዳት ምክንያት ለጨዋታ ዝግጁ እንዳልሆነ የተገለፀው አቤል ማሞ በጨዋታው የመሰለፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

በወላይታ ድቻ በኩል በጉዳት የአሸናፊዎች አሸናፊ እና የሊጉ የመጀመርያ ጨዋታ ያመለጠው በዛብህ መለዮ ከጉዳቱ ማገገሙ ለቡድኑ ጥሩ ዜና ነው፡፡ እሸቱ መና በብሔራዊ ቡድን ጉዞ ምክንያት ጨዋታው ሲያመልጠው በክረምቱ ክለቡን የተቀላቀለው ናይጄርያዊው አማካይ ሂለሪ ኢኬና የዝውውር ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ ባለመጠናቀቁ ለጨዋታው ተገቢ ያልሆነ ተጫዋች ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *