​የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ሳምንት የቅዳሜ ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ በዓዲግራት ፣ ወልድያ እና አዲስ አበባ በሚደረጉ ሦስት ጨዋታዎች የሚጀምር ይሆናል። በነዚህ ጨዋታዎች ላይ የሚነሱ ነጥቦችንም እንደሚከተለው አሰናድተናቸዋል።

ወልድያ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በሊጉ ጅማሮ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የነበረው ጨዋታ ወደሌላ ጊዜ የተላለፈበት ድሬደዋ ከተማ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋርን በሜዳው 1-0 በመረታት አመቱን ጀምሯል። ይህ በመሆኑም የነገው ጨዋታ ከሜዳው ውጪ የሚያደርገው የመጀመሪያ ጨዋታ ይሆናል። ተጋጣሚው ወልድያ በበኩሉ በመጀመሪያው ሳምንት ሜዳው ላይ አዳማ ከተማን በማስተናገድ እና 2- 0 መርታት ቢችልም በሳምንቱ ሀዋሳ ላይ በሀዋሳ ከትማ 4-1 መረታቱ አነጋጋሪ ሆኗል።

ሁለቱም ቡድኖች በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የተሳተፉ ቢሆንም በጨዋታ አቀራረቡ ለውጥ የታየበት ግን ወልድያ ነው። አምና ሜዳው ላይ ካደረጋቸው ጨዋታዎች መሀከል በአንድ አጋጣሚ ብቻ ሀለት ግቦችን ያስቆጠረው ወልድያ ዘንድሮ ገና በመጀመሪያ ጨዋታው በሁለት ግቦች ማሸነፉ ለዚህ ነጥብ አንዱ ማሳያ ነው። በተቃራኒው ከሜዳ ውጪ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች ጥንቃቄ በተሞላበት አቀራረብ የሚያደርገው ድሬደዋ ከተማ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታውን ማሸነፍ መቻሉ በዚህኛው ጨዋታ አንድ ነጥብ ማሳካት ላይ ትኩረት እንዲያደርግ የሚጋብዘውም ይሆናል። በመሆኑም ብርቱካናማዎቹ ለተከላካይ ክፍሉ በጣሙን የተጠጋ የአማካይ ክፍል እና መሀል ሜዳ አካባቢ በሚታዩ የፊት አጥቂዎች ወልድያን እንደሚገጥሙ ይጠበቃል። በዚህም መሰረት የአሰልጣኝ ዘመራያም የአጥቂ አማካዮች ከድሬደዋ የአማካይ ክፍል ጀርባ ለመግባት ለአጥቂዎች የመጨረሻ ኳሶች በማድረሱ በኩል የሚፈተኑበት ጨዋታ ይሆናል። አምና የሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስቴድየም የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታ ላይ ተገናኝተው ያለግብ የተለያዩት ሁለቱ ቡድኖች በነገው ጨዋታ ላይም በተመሳሳይ መልኩ ሊለያዩ እንደሚችሉ በብዙዎች ተገምቷል።

በወልድያ በኩል የመሀል ተከላካዩ አዳሙ መሀመድ በጉልበት ጉዳት ምክንያት የማይሰለፍ ሲሆን ድሬደዋ ከተማም ወሰኑ ማዜ እና ሀብታሙ ወልዴን በጉዳት እንዲሁም አህመድ ረሻድን በቅጣት የማይጠቀም ይሆናል።

ይህን ጨዋታ ፌደራል ዳኛ አሰፋ ደቦጭ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ ሲዳማ ቡና

አዲስ አዳጊው ወልዋሎ ሳምንት ከከፍተኛ ሊጉ ካደገው ሌላው ክለብ መቐለ ከተማ ጋር ያለግብ አቻ የተለያየ ሲሆን በመጀመሪያው ሳምንትም ሜዳው ላይ ፋሲል ከተማን አስተናግዶ በሁለት ግቦች ልዩነት መምራት ቢችልም በሁለተኛው አጋማሽ ባስተናገዳቸው ሁለት ግቦች ነጥብ ለመጋራት ተገዷል። አምና በሊጉ ብርቱ ተፎካካሪ የነበረው ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የነበረው የመጀመሪያው ጨዋታው ከተላለፈ በኃላ አርባምንጭ ከተማን በሜዳው አስተናግዶ ነጥብ በመጋራት ሊጉን ጀምሯል።

በሁለት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ማሳካት የቻለው ወልዋሎ ዓ.ዩ በቡድን ግንባታው ላይ ብዙ የሚቀረው ቢሆንም ለማጥቃት ቅድሚያ የሚሰጥ አይነት ቡድን መሆኑ ግን ካለፉት ጨዋታዎቹ መረዳት ይቻላል። ሆኖም በተለይ በመቐለው ጨዋታ ላይ እንደተመለከትነው ከተከላካይ አማካዩ ፊት የሚሰለፉ ሁለቱ አማካዮች የሚኖራቸው የተጠጋጋ የጨዋታ ላይ እንቅስቃሴ የቡድኑ የመሀል ሜዳ ቅብብሎች የተጋጣሚን የአማካይ እና የተከላካይ ክፍል ለመሰንጠቅ አቅም እንዳይኖራቸው ሲያደርግ ታይቷል። ይህም ቡድኑ በተለይ እንደ ሲዳማ ቡና ካለ በርከት ያሉ አማካዮችን ከሚጠቀም እና ከሜዳው ውጪ ሲጫወት በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ ከሆነ ቡድን ጋር  ሲጫወት እንዲቸገር ሊያደርገው የሚችል ጉዳይ ነው። የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ በብዛት የተመሰረተበት ፕሪንስ ሰቨሪንሆ እና ሌላው የመስመር አጥቂ አብዱርሀማን ፉሴኒ ከሙላለም ጥላሁን ጋር የሚኖራቸው ጥምረት በዚህ ጨዋታ ለቢጫ ለባሾቹ እጅግ ወሳኝ እንደሚሆን ይጠበቃል። ከአርባ ምንጩ ጨዋታ አንድ ነጥብ ያገኙት ሲዳማዎች ከነገውም ጨዋታ ተመሳሳይ ውጤት ቢያገኙ የሚጠሉ አይመስልም። ምንም እንኳን አምና የነበረው የመከላከል ጥንካሬ ላይ ይገኛል ብሎ ለመናገር ቢከብድም ሲዳማ ቡና በጨዋታው በቀላሉ ክፍተት ላለመስጠት ወደሜዳ እንደሚገባ ይታሰባል። ሆኖም ቡድኑ  በመልሶ ማጥቃት የሚገኙ ዕድሎችን ለመጠቀም እንደ አዲስ ግደይ እና ባዬ ገዛሀኝ አይነት ፈጣን ተጨዋቾችን መያዙ በጨዋታው ግብ ለማስቆጠር የሚረዳው እንደሚሆን ይጠበቃል።

በሲዳማ ቡና በኩል የተሰማ የጉዳት ዜና ባይኖርም የወልዋሎ ዓ.ዩው የግራ መስመር ተከላካይ ሮቤል ግርማ ከጉዳት ሲመለስ የመሀል አማካዩ ብሩክ አየለ እና ተስፋዬ ዲባባ በመቐለው ጨዋታ ባስተናገዱት ጉዳት ምክንያት ይህ ጨዋታ የሚያልፋቸው ይሆናል።

ፌደራል ዳኛ አዳነ ወርቁ የሁለቱን ቡድኔች ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ መከላከያ

አዲስ አበባ ስቴድየም ላይ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሲጀምር  ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ቡና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የነበረውን ጨዋታ ከተላለፈ በኃላ የአመቱን የመጀመሪያ ጨዋታውን ከመከላከያ ጋር ያደርጋል። መከላከያ በበኩሉ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ በመጋራት እና በወላይታ ድቻ 1-0 በመረታት አመቱን መጀመሩን ተከትሎ የነገው ጨዋታ በድኑ ከገባበት የውጤት ማጣት ሂደት ለማገገም የሚያደርገው ጨዋታ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያሳካው እና የሜዳ ላይ የቡድኑ ውህደትም አጥጋቢ ደረጃ ላይ የማይገኘው መከላከያ በነገው ጨዋታ ሊቸገር እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ይቻላል። ሚካኤል ደስታን ያጣው የጦሩ የአማካይ ክፍል ሚዛን ማጣት እና የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ሀላፊነቱ በአመዛኙ በመስመር አማካዮቹ ላይ የተጣለ መሆኑ ጨዋታውን ይበልጥ ያከብድበታል። በተለይ ከተከላካይ አማካዩ ፊት ለፊት ባለው የሜዳ ክፍል ላይ ለተጋጣሚ ቡድን የኳስ መቀባበያ ክፍተቶችን የሚተወው መከላከያ የነገ ተጋጣሚው የኢትዮጽያ ቡና ይህን ክፍተት መጠቀም የሚችሉ አማካዮችን የያዘ መሆኑ ይበልጥ ተጋላጭ ያረገዋል። በአሰልጣኝ ፓፒች ስር የመጀመሪያ ጨዋታውን የሚያደርገው ኢትዮጵያ ቡና አማካይ ክፍል ላይ በመስዑድ መሀመድ እና ሳምሶን ጥላሁን አማካይነት የመከላከያን ደካማ ጎን ለመፈተን እንደሚችል ይታሰባል። በንፅፅር ወደ እነምንይሉ ወንድሙ የተሻሉ ኳሶችን የሚያደርሰው የመከላከያ የመስመር እንቅስቃሴም ከኢትዮጵያ ቡና የማጥቃት ባህሪ ያላቸው የመስመር ተከላካዮች የሚገናኝባቸው ሁለቱ መስመሮችም እንዲሁ በጨዋታው ተጠባቂ እንቅስቃሴ ከሚታይባቸው የሜዳ ክፍሎች መሀከል ይጠቀሳሉ። አምና በሊጉ ሁለተኛ ሳምንት ተገናኝተው የነበሩት ሁለቱ ክለቦች ማራኪ በነበረ ጨዋታ 2-2 መለያየታቸው የሚታወስ ነው።

በቤሔራዊ ቡድኑ ጨዋታ ላይ ጉዳት ያስተናገደው አስቻለው ግርማ ይህ ጨዋታ የሚያፈው ሲሆን ማራኪ ወርቁ ፣ አዲሱ ተስፋዬ እና አቅሌስያስ ግርማን በጉዳት የማያሳልፈው መከላከያ ከጉዳት የተመለሰውን የሳሙኤል ታዬን አገልግሎት እንደሚያገኝ ይጠበቃል።

ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ ሐይለየሱስ ባዘዘው  በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *