​የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ወደ ጥቅምት 2018 ተራዝመዋል

ካሜሩን ለምታስተናግደው የ2019 የቶታል አፍሪካ ዋንጫ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች በመጋቢት ወር እንዲካሄዱ መርሃ ግብር ወጥቶላቸው የነበረ ቢሆንም የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ራባት ላይ ባደረገው ስብሰባ መሰረት የማጣሪያ ጨዋታዎቹ ወደ ጥቅምት 2018 እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡

የመርሃ ግብር ቀን ለውጥ የተደረገው ሩሲያ በምታስተናግደው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑት አምስት የአህጉሪቱ ሃገራት በቂ የዝግጅት ግዜ እንዲኖራቸው ታስቦ ነው፡፡ ናይጄሪያ፣ ሞሮኮ፣ ሴኔጋል፣ ግብፅ እና ቱኒዚያ በመጋቢት ወር በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከመጫወት ይልቅ በአቋም መለኪያ ጨዋታዎች እራሳቸው ለዓለም ዋንጫው የሚያዘጋጁ ይሆናል፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ ከ2019 አንስቶ በሰኔ/ሃምሌ ወር የሚካሄድ በመሆኑ ከጥቅምት 2018 ጀምሮ የማጣሪያ ጨዋታዎች ቢደረጉም የሰፋ ግዜ በመኖሩ የፕሮግራም መጣበብ እንደማይከሰት ተነግሯል፡፡

ኢትዮጵያ በምድብ ስድስት ከጋና፣ ሴራ ሊዮን እና ኬንያ ጋር የተደለደለች ሲሆን የመጀመሪያ ጨዋታዋን ኩማሲ ላይ በጋና 5-0 መሸነፏ አይዘነጋም፡፡ ኢትዮጵያ ቀጣይ ጨዋታዋን በመጋቢት ወር ሴራ ሊዮንን በሜዳዋ የምታስተናግድ የነበረ ቢሆንም በለውጡ ምክንያት ጨዋታዎ ቀን ተራዝሟል፡፡ ይህንን ተክትሎም ብሄራዊ ቡድን ከህዳር 24 ጀምሮ ከሚሳተፉበት የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ መልስ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን የወዳጅነት ጨዋታዎችን ካላዘጋጀ በቀር ብሄራዊ ቡድንኑ የምናይበት እድል እጅግ በጣም የጠበበ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *