ሪፖርት | አዳማ ከተማ በሜዳው የመጀመሪያውን ድል አስመዘገበ

ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መሀከል አንዱ የነበረው የአዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ በኤፍሬም ዘከሪያስ ብቸኛ ጎል በአዳማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ባለሜዳዎቹ አዳማዎች ባልተጠበቀ ሁኔታ ቡልቻ ሹራን እና ኤፍሬም ዘካሪያስን በቋሚ አሰላለፋቸው ውስጥ አካተው ከቅጣት የተመለሰው ሱሊማን መሀመድንም አማካይ መስመር ላይ በመጠቀም ነበር ጨዋታውን የጀመሩት። ሀዋሳ ከተማዎችም ዳዊት ፍቃዱን እና ደስታ ዮሀንስን በጉዳት ባልያዙበት ቡድን ውስጥ ለጌትነት ቶማስ ፣ ፀጋአብ ዮሴፍ እና ነጋሽ ታደሰ የመጀመሪያ የመሰለፍ ዕድል አግኝተዋል።

የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበባቸው ነበሩ። ሆኖም የግብ ሙከራዎችን ለመመልከት የተቻለው ከ13ኛው ደቂቃ በኃላ ነበር። በዚሁ ደቂቃ ሀዋሳ ከተማዎች በቀኝ መስመር ባገኙት ክፍተት ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን ይዞ የገባውን ኳስ ቀለል ባለ ምት ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ ጃኮ ፔንዜ ይዞበታል። ከዚህ ሙከራ ከአንድ ደቂቃ በኃላ ሁለቱም ቡድኖች በጉዳት ምክንያት ቅያሪዎችን አድርገዋል። በዚህም በሀዋሳ በኩል ላውረንስ ላርቴ ወጥቶ ወንድማገኝ ማዕረግ ሲገባ የአዳማው የፊት መስመር አጥቂ ቡልቻ ሹራም በበረከት ደስታ ተተክቷል። በሱራፌል ዳኛቸው ምርጥ እንቅስቃሴ መነሻነት አዳማዎች የፈጠሩት ዕድል በሀዋሳዎች መክኖባቸው የተገኘውን የማዕዘን ምት አዲስ ህንፃ ሲያሻማ በክረምቱ ሀዋሳን ለቆ አዳማን የተቀላቀለው ኤፍሬም ዘካሪያስ በግንባሩ አስቆጥሯል።

ከጎሉ በኃላ የአዳማዎች የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ የግብ ዕድልን የፈጠረ ባይሆንም በተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫ የወሰደ ነበር። ሆኖም 33ኛው ደቂቃ ላይ ሱሌይማን መሀመድ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ኤፍሬም በግንባሩ ሞክሮ ሶሆሆ ካወጣበት ሌላ አስደንጋጭ ሙከራ አላደረጉም። ደቂቃዎች በገፉ ቁጥርም ሀዋሳዎች የበላይነቱን ወስደው ባለሜዳዎቹ ወደኃላ ተገፍተው ታይተዋል። የሀዋሳዎች የበላይነትም ቢሆን ግን በግብ ሙከራዎች የታጀበ አልነበረም ቡድኑ ያገኛቸው በርካታ የማዕዘን ምቶችም ሲባክኑ እንጂ ወደ ሙከራነት ሲቀየሩ አልታዩም። በአንድ አጋጣሚ ብቻ ከማዕዘን ምት የተመለሰችን ኳስ ፀጋአብ ከርቀት አክርሮ ሞክሮ ፔንዜ ሲያወጣበት ተስተውሏል። ፈጠን ብሎ የጀመረው የመጀመሪያ አጋማሽም እየተቀዛቀዘ መጥቶ ከመሀል የሚነሱ የቆሙ ኳሶች በርክተውበት ተገባዷል።

ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረባቸው ደቂቃዎች ሀዋሳዎች ይበልጥ ተጭነው ለመጫወት ሲሞክሩ ታይተዋል። የተሻለ የኳስ ቁጥጥርን ይዘው የነበሩት ሀይቆቹ አብዛኛው የኳስ ፍሰታቸው በአዳማዎች የሜዳ ክፍል ላይ ያረፈ ነበር ። 51ኛው ደቂቃ ላይ ከታፈሰ ሰለሞን የተነሳን ኳስ ያቡን ዊልያም በግሩም ሁኔታ አቀብሎት የቀኝ መስመር አጥቂው ፍቅረየሱስ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ሙከራው ወደላይ ተነስቷል። 58ኛው ደቂቃ ላይም ጂብሪል አህመድ ከርቀት በቀጥታ የመታት የቅጣት ምት ከመሬት ጋር ነጥራ ወደግብ ብታመራም በጃኮ ፔንዜ ጥረት ግብ ከመሆን ድናለች። ከዚህ በኃላ ሁለተኛውን አጋማሽ በመጠኑ አፈግፍገው የጀመሩ መስለው የነበሩት አዳማዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ማስመለስ ባይችሉም ሀዋሳዎችን ከግብ ክልላቸው ርቀው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ አልተሳናቸውም። በተወሰኑ አጋጣሚዎችም የሀዋሳ ከተማን የተከላካይ መስመር መዘናጋት በመጠቀምም ሰብረው ለመግባት ሲሞክሩ ታይተዋል። በተለይ 74ኛው ደቂቃ ላይ ሲሳይ ቶሊ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ውስጥ በተሻማው ኳስ ሶሆሆ እና የሀዋሳ ተከላካዮች መሀል አለመናበብ ሲፈጠር አግኝቶ ሁለተኛ ጎል ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። ሆኖም አብዛኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሀይል የተቀላቀለ ጨዋታን አስተናግዶ ግጭቶችን ተከትለው በሚሰጡ የህክምና እርዳታዎችና የቅጣት ምቶች እየተቆራረጠ የተጠናቀቀ ነበር። በውጤቱም አዳማ ከተማ በሜዳው የመጀመሪያ ድሉን ሲያጣጥም ሀዋሳ ከተማ ሶስተኛ ተከታታይ የሜዳ ውጪ ሽንፈት አስተናግዷል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

ም/አሰልጣኝ አስቻለው ሀ/ሚካኤል – አዳማ ከተማ

” ጨዋታው ተመጣጣኝ ነበር። ያገኘነውን ዕድል ተጠቅመን ሶስት ነጥብ ይዘን መውጣት ችለናል። ለመሸናነፍ በነበረው ትግልም ጨዋታው ትንሽ ሀይል የቀላቀለ ነበር። በርካታ ተጨዋቾች በተለይ በአማካይ እና አጥቂ ክፍል ላይ ተጎድተውብናል። በቀጣይ እነሱ ሲመለሱ በማጥቃቱ በኩል ያለው መሳሳት የሚቀረፍ ይሆናል። ”

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ- ሀዋሳ ከተማ

” የመሀል ተከላካያችን በጉዳት ከሜዳ ወጥቶ ወደ ሆስፒታል ሄዷል። ከዛ በኃላም ከጨዋታው ይልቅ ግጭቶች በርክተው ነበር ። ጨዋታውን ለመቆጣጠር ጥረት አድርገናል። ከዛ ውጪ የቆሙ ኳሶችን በመከላከሉ ረገድ ድክመት ነበረብን። ጎሉም የገባው ከቆመ ኳስ መነሻነት ነበር። በተረፈ ከእስካሁኑ የተሻለ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *