​ዩራጓይ 2018 | ኢትዮጵያ በሜዳዋ አቻ ተለያይታ የማለፍ ተስፋዋን አደብዝዛለች

ለ2018 የአለም ከ17 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ ለማለፍ በአፍሪካ ዞን የመጀመርያ ዙር ማጣርያ ናይጄርያን የገጠመው የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ በአ.አ ስታድየም የመጀመርያ ጨዋታውን (First Leg) አድርጎ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሙከራ እና በጨዋታ እንቅስቃሴ ተሸሎ ሲታይ በሙከራ ረገድም ቀዳሚ መሆን ያቻሉት ታዳጊዎቹ ሉሲዎች ነበሩ። ትመር ጠንክር ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን በመግባት ወደ ግብ የመታችውን ኳስ በግብ ጠባቂዋ ክሪስትና ከሽፎባታል። በ17ኛው ደቂቃ ላይ ኪፊያ አብዱራህማን ወደ ግብ አክርራ የመታችውና በግቡ አናት የወጣው ሙከራም ኢትዮጵያን ቀዳሚ ሊያደርግ የሚችል ነበር።

ጥንቃቄ የተሞላበትን እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት ናይጄርያዎች በ18ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ዩቱንድ በቀኝ ክንፍ በኩል ያሻገረችውን ኳስ በነፃ አቆቀም ላይ የነበረችው ፕሪሽየስ ቪንሰንት አማካኝነት ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ከግቡ መቆጠር በኃላ ናይጄርያዎች መነቃቃት የተየባቸው ሲሆን በ20ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ፕሪሽየስ በድጋሚ አግኝታ ሌላኛውን ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርጋ ነበር፡፡ 

ኢትዮጵያ ለተቆጠረው ግብ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የጎል ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። በተለይም በ22ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ትመር ጠንክር ያሻማችውን ኳስ ረድኤት አስረሳኸኝ አግኝታ የሞከረችውና በግቡ በስተግራ በኩል የወጣባት ፤ በ31ኛው ደቂቃ ላይ ረድኤት አስረሳኸኝ ከመሀል ሜዳ የተሻገረትን ኳስ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥራ ከግብ ጠባቂዋ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝታ አክርራ በመምታት በግቡ በስተቀኝ በኩል የወጣባት እንዲሁም በ42ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት ረድኤት አስረሳኸኝ መትታ በግብ ጠባቂዋ ክሪስቲና በቀላሉ የተመለሰባት ሙከራዎች ኢትዮጵያ የአቻነት ጎል ለማግኘት ካደረጓቸው ሙከራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

ከዕረፍት መልስ ናይጄሪያዎች በማጥቃት ሂደት ላይ ሲሆኑ በ4-3-3 እንዲሁም ወደ መከላከል ሲሸጋገሩ 4-5-1 በሆነ ቅርፅ ሲጠቀሙ ተስተውለዋል፡፡ 60ኛው ደቂቃ ላይ ፕሪኮስ ለብቻዋ ያገኘችውን ኳስ አባይነሽ ያዳነችባት ሲሆን የ75ኛው ደቂቃ የጆይ ጂሪ መከራም በተመሳሳይ በግብ ጠባቂዋ የተመለሰ ነበር፡፡ ናይጄሪያዎች በፈጠሩት ሌላ ዕድልም 81ኛው ደቂቃ ላይ ፌቨር ኤማኑኤል ከማዕዘን የታሻገረውን ኳስ በጭንቅላቷ ገጭታ ስትሞክር በግቡ አናት ወጥቶባታል፡፡ 

ከዕረፍት መልስ አጥቅተው እና ኳስ ተቆጣጥረው የተጫወቱት ሉሲዎቹ በ55ኛው ደቂቃ ላይ በትመር አማካይነት ያደረጉት ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቢቀርም ከስምንት ደቂቃዎች በኃላ ግን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም 63ኛው ደቂቃ ላይ እመቤት አዲሱ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ  በቀኝ በኩል የተገኘውን ቅጣት ምት ታሪኳ ደቢሶ ወደ ግብ አክርራ በመምታት የአቻነቷል ግብ አስቆጥራለች፡፡ ከግቡ መቆጠር በኃላ መነቃቃት የታየባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ  ቡድን ተሰላፊዎች በተደጋጋሚ ወደ ናይጀሪያ ግብ ክልል ሲደርሱ የቆዩ ሲሆን 86ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካሳ የሞከረችው ሙከራ በግቡ ዓናት ወጥቶባታል፡፡ በዚህም መልኩ የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ተገባዷል። የመልሱ ጨዋታም በቀጣዩ ሳምንት በናይጄሪያ ሜዳ የሚደረግ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *