ደደቢት የቀድሞ ተከላካዩን የግሉ አድርጓል፡፡ አይናለም ኃይለ ከዳሽን ጋር የበረው የ2 አመት ኮንትራት ዘንድሮ የተጠናቀቀ ሲሆን ከሳምንታት በፊት ጀምሮ ከደደቢት ጋር ድርድር ሲያደርግ እንደነበር ተነግሯል፡፡
ዛሬ ከክለቡ ባገኘነው መረጃ መሰረትም ደደቢት ተከላካዩን ለሁለት አመታት ውል አስፈርሞታል፡፡ ክለቡ የፊርማውን ዋጋ ከማሳወቅ የተቆጠበ ሲሆን በወቅታዊው የገብያ ዋጋ መፈረሙ ተነግሯል፡፡
አይናለም በክለብ ህይወቱ እውቅና ማግኘት የጀመረው በመከላከያ በነበረበት ወቅት ነበር፡፡ በ2003 ክረምት መከላከያን ለቆ ለደደቢትን የተቀላቀለው አይናለም በሰማያዊዎቹ ቤት ባሳየው ብቃት የብሄራዊ ቡድን ቋሚ ተሰላፊነትን አስገኝቶለት ነበር፡፡ በ2005 ደደቢት ላሳካው የፕሪሚየር ሊግ ድል ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች አንዱ የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ እድታልፍ ካደረጉ ተጫዋቾች መካከልም ነበር፡፡
በ2005 ክረምት ደደቢትን ለቆ በወቅቱ የሪኮርድ ክፍያ በ1.1 ሚልዮን ዳሽን ቢራን ከተቀላቀለ በኋላ ቡድኑን በአምበልነት ሲመራ ቆይቷል፡፡
የአንጋፋው ተከላካይ ወደ ደደቢት መመለስ በአስቻለው ታመነ መልቀቅ የሚፈጠረውን ክፍተት ለመድፈን ያስችላል ተብሎለታል፡፡ አስቻለው ታመነ ክለቡን ለቆ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለመፈረም የተስማማ ቢሆንም እስካሁን በይፋ ለክለቡ ፊርማውን አላኖረም፡፡