ወልዲያ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ | ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ወልዲያን ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያገናኝ ይሆናል። ዛሬ 09፡00 ሰዐት ላይ በሼክ መሀመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታዲየም የሚደረገውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ፌደራል ዳኛ ተፈሪ አለባቸው በመሀል ዳኝነት የሚመሩት የዛሬው ጨዋታ ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች ያሏቸው ቡድኖች እርስ በእርስ የሚገናኙበት ይሆናል። ሊጉ አሁን ላይ ከሚታይበት የነጥብ ቅርርብ አንፃርም ቡድኖቹ ባላቸው ቀሪ ጨዋታዎች ውጤት ማግኘት ከቻሉ እሰከ ሊጉ አናት የመጠጋት አቅም ያላቸው ናቸው። ሌላው የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ሁለቱም አራት ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ማጠናቀቃቸው ነው። ሆኖም ሽንፈት ያላስተናገደው እና የተሻለ የማሸነፍ ንፃሬ ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ በደረጃ ሰንጠረዡ ከተጋጣሚው ወልድያ በርቀት ከፍ ብሎ ተቀምጧል። አምና 25ኛው ሳምንት ላይ ሲገናኙም ቅዱስ ጊዮርጊስ ነበር በአብዱልከሪም ኒኪማ ብቸኛ ጎል ባለድል መሆን የቻለው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተፎካካሪው ደደቢት ላለመራቅ ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ሆኖም አራተኛው እና አምስተኛው ሳምንት ላይ በተከታታይ ካሸነፈበት አጋጣሚ በኃላ የአቻ ውጤቶችን ሲያስመዘግብ ተስተውሏል። የዛሬው ጨዋታም ቡድኑ ጨዋታውን በማሸነፍ 10ኛው ሳምንት ላይ ያገኘውን ድል ለማስቀጠል የሚያደርገው እንደሚሆን ይጠበቃል። እስካሁን ያገኛቸውን ሁለት ድሎች ሜዳው ላይ ያሳካው ወልድያ በሜዳው መረቡን ባለማስደፈት ጭምርም ነው ለዚህ ጨዋታ የደረሰው። በኢትዮጵያ ቡና ከደረሰበት ሽንፈት በቶሎ በማገገም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን የሰበሰበው ወልድያ ይህን ጨዋታ አሸንፎ ወደ ሰባተኛ ደረጃ ከፍ ለማለት ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል።

ከወልዋሎ ዓ.ዩ ጋር በነበረው ጨዋታ የመጀመሪያውን አጋማሽ ብቻ የተጫወተው አዳሙ መሀመድ እና በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ተስፋዬ አለባቸው እንዲሁም ሌላኛው የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች ምንያህል ተሾመ የመሰለፋቸው ነገር አጠራጣሪ ሆኗል። ከዚህ ውጪ ብሩክ ቃልቦሬ እና አማረ በቀለ ቅጣት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በጅማ አባ ጅፋሩ ጨዋታ ያልተሰለፈው አብዱልከሪም ኒኪማ እና በዚሁ ጨዋታ ጉዳት የገጠመው ኢብራሂማ ፎፋና ልምምድ እየሰሩ በመሆኑ ለወልድያው ጨዋታ የመድረስ ዕድል ይኖራቸዋል። ከሳላዲን ሰይድ ፣ አሜ መሀመድ ፣ ታደለ መንገሻ እና ናትናኤል ዘለቀ ሌላም የተሰማ አዲስ የጉዳት ዜና የለም።

ባለሜዳዎቹ ወልድያዎች ከኢትዮጵያ ቡና እና ወልዋሎ ዓ.ዩ ጋር ያደረጓቸው ጨዋታዎች ቡድኑ የአማካይ ክፍል ላይ የበላይነት በሚወሰድበት አጋጣሚ በእጅጉ እንደሚዳከም ያሳዩ ነበሩ። የወልድያ አንደኛው ጥንካሬ የሆነው ኤሚክሪል ቤሊንጌ ተደጋጋሚ ሙከራዎች በሚያስተናግድባቸው አጋጣሚዎች የተከላካይ ክፍሉ የተጋጣሚን ጥቃት አፍኖ እንዳያስቀር የአማካዮቹ እገዛ ደካማ የሚባል ነው። ቡድኑ በሚጠቀምበት የ4-2-3-1 አሰላለፍ ውስጥ በመስመር አማካይነት እንዲሁም አጨዋወቱ ወደ 4-3-3 የቀረበ ሲመስል በመስመር አጥቂነት የሚሰለፉ ተጨዋቾች የጨዋታ ባህሪን ተከትሎ ያላቸው አናሳ የመከላከል ተሳትፎ  ለዚህ የቡድኑ ድክመት ዋነኛ መንስኤ ነው። ከአማካዮቹ አንዱ የሆነው ምንያህል ተሾመም ተመሳሳይ የጨዋታ ባህሪን የተላበሰ ሲሆን ለተከላካይ አማካዩ ቀርቦ የሚጫወተው ሐብታሙ ሸዋለምም በማጥቃት እና በመከላከል ሂደቱ መሀል ሲዋልል ይታያል። የብሩክ ቃልቦሬ ቅጣት እና የተስፋዬ አለባቸው ሙሉ ጤና ላይ አለመገኘት ደግሞ ለተከላካይ አማካዩ ሽፋን የሚሰጥ ሁነኛ ተጨዋች እንዳይኖር በማድረጉ ቡድኑ መሀል ለመሀል የሚሰነዘርበትን ጥቃት ቀድሞ በመከላከል ረገድ እንዲዳከም ሆኗል። ይህ ክፍተት ተጋጣሚዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በቀላሉ እንዲያገኙ ከማድረጉም በላይ ቡድኑ በመልሶ ማጥቃት የሚያገኛቸውን ዕድሎች ለመጠቀም ሲሞክር በሚወሰድባቸው ብልጫ ከተጋጣሚ ግብ በእጅጉ ርቀው የሚታዩት አጥቂዎች ቦታ አያያዝ ፍሪያማ እንዳይሆን ሲያደርገው ይታያል። በዛሬው ጨዋታ የተከላካይ ክፍሉን ወደፊት ገፍቶ የሚጫወተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመልሶ መጠቃት የተጋለጠ ቢሆንም የወልድያ አጥቂዎች ይህን ደካማ ጎን ሊጠቀሙበት ይችላሉ ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳው ምቹነት እና መሀል ሜዳ ላይ ያለጫና ከሚያገኘው ክፍተት አንፃር እንደ አባ ጅፋሩ ጨዋታ ሁሉ ለኳስ ቁጥጥሩ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ይጠበቃል። ቡድኑ በዚህ ሂደት ውስጥ የመስመር አጥቂዎቹን ተሳትፎ የሚያክልበት ከሆነ በተጋጣሚው ላይ የበላይነት ለመውሰድ የሚቸገር አይሆንም። ይህን ለማድረግ ግን በፊት አጥቂ ቦታ ላይ የሚሰለፈው ተጨዋች በሁሉም አቅጣጫዎች ያለኳስ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አጋዥነቱ ከፍ ያለ ነው። በዋነኝነት የወልድያ የፈጠራ ምንጭ የሆነው ምንያህል ተሾመን ከጨዋታ ውጪ በማድረጉ እና የቡድኑን የኳስ ስርጭት በመምራት በኩል ሙሉአለም መስፍን ከፍ ያለ ሀላፊነት ሲኖርበት የአጥቂ አማካይነት ሚና እንደሚኖራቸው የሚጠበቁት ምንተስኖት አዳነ እና አብዱልከሪም ኒኪማ ደግሞ ከላይ በተጠቀሰውን የወልድያ የአማካይ ክፍል የመከላከል ሽግግር ድክመት ለመጠቀም ቅብብሎቻቸው ስኬታማና ፈጣን መሆን ይኖርባቸውዋል። ጨዋታው ለፈረሰኞቹ ፈታኝ የሚሆነው ወልድያ የአማካይ ክፍሉን አወቃቀር በማስተካከል ለተከላካይ መስመሩ ቀርቦ እንዲጫወት የሚያደርግ ከሆነ ነው። በቀደሙት ጨዋታዎች እንዳስተዋልነው ቅዱስ ጊዮርጊስ መሰል ተጋጣሚዎች ሲያጋጥሙት የኳስ ቁጥጥሩ ክፍተቶችን ለማግኘት እና የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር አቅም ያጣል። በመሆኑም በተለይ ግብ ሳያስቆጥር የጨዋታውን የመጀመሪያ አንድ ሰዐት ካገባደደ ከተከላካይ ክፍሉ እና ከሁለቱ መስመሮች የሚነሱ ረዣዥም ኳሶች ዋነኛ የሙከራ ምንጮቹ ይሆናሉ። ኤሚልሪል ቤሊንጌ ከሁለቱ የመሀል ተከላካዮቹ ጋር በመሆን እነዚህን ኳሶች በማዳኑ በኩል የሚሳካለት ከሆነ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ግብ በቀላሉ የማያገኙበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *