​ሪፖርት | ወልዲያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ተጋርተዋል

የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት የመጀመርያ ጨዋታ ወልዲያ በሼክ መሀመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲን ስታድየም ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግዶ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ወልዲያ አአ ስታድየም ላይ ከወልዋሎ 0-0 ከተለያየበት የቡድን ስብስብ መካከል ጉዳት ያስተናገደው አዳሙ መሐመድን በብርሃኔ አንለይ ፣ አጥቂው ኤደም ኮድዞን በዓንዱአለም ንጉሴ በመተካት 4-3-3 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምረዋል። በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች አአ ስታድየም ላይ ጅማ አባጅፋርን 3 – 0 ከረቱበት ስብስባቸው ምንም አይነት የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ በተመሳሳይ 4-3-3 ጨዋታውን ጀምረዋል።

ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በአመቱ ከፍተኛ የሆነ ተመልካች በተስተናገደበት በዚህ ጨዋታ ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ የወልዲያ ስራ አስኪያጅ አቶ ገረመው ለቅዱስ ጊዮርጊስ የቡድን መሪ ባዩ ሙሉ የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርከተዋል።

በተፈሪ አለባቸው የመሀል ዳኝነት በተጀመረው ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ በሁለቱም በኩል አይፈጠር እንጂ የጨዋታው እንቅስቃሴ የኳስ ፍሰቱ ጥሩ የሚባል ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ ግን የጨዋታውን እንቅስቃሴ የሚቆራርጡ አላስፈላጊ ጥፋቶች እና ጉሽሚያዎች እንዲሁም አወዛጋቢ ውሳኔዎች ተከስተው አልፈውበታል። 16ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን ፍፁም ገ/ማርያም ከቀኝ መስመር ኳስ እየገፋ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ሳጥን ውስጥ ገብቶ አብዱልከሪም መሀመድን አልፌ እሄዳለው ሲል ጥፋት ቢሰራበትም ጨዋታውን መቆጣጠር ከብዷቸው የዋሉት ፌደራል ዳኛ ተፈሪ አለባቸው ሆን ብለህ ወድቀሀል በሚል በዝምታ ማለፋቸውን ተከትሎ የወልድያ የቡድን አባላት ተቀያሪ ወንበር ላይ የተቀመጡትን ጨምሮ በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። በተለምዶ ካታንጋ በሚባለው የስታድም ክፍል የነበሩ ደጋፊዎችም ወደ ረዳት ዳኛው የተለያዩ ቁሳቁስን በመወርወራቸው ጨዋታው ለ3 ደቂቃ ያህል ሲቋረጥ ወልድያዎችም ፍ/ቅ/ምቱ መከልከሉ ተገቢ አይደለም በሚል የክስ ሪዘርቭ አስይዘዋል።

ከአወዛጋቢው ክስተት በኋላ በቀጠለው ጨዋታ ምንም እንኳን ጠንካራ ለጎል የቀረበ ሙከራ ባይደረግበትም ጥሩ የኳስ ፍሰት እና ማራኪ የጨዋታ እንቅስቃሴ መመልከት ችለናል። ሆኖም በተደጋጋሚ በሚሰሩ አላስፈላጊ ጥፋቶች ምክንያት የዕለቱ ዳኛ ተፈሪ አለባቸው ፊሽካ ባሰሙ ቁጥር ተጫዋቾች ዳኛን የመክበብ ፣ የማዋከብ ፣ ግርግር የመፍጠር ሁኔታ የጨዋታውን መልክ እየቀየረው የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በርካታ የጎል ሙከራ የተደረገበት ሲሆን በተለይ እንግዶቹ ፈረሰኞቹ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ አጋጣሚዎች የፈጠሩበት ሆኖ አልፏል። 54ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ሳኒ በበኃይሉ አሰፋ አማካኝነት የተጣለለትን ኳስ ግብ ጠባቂው ቤሊንጌን አልፌ ጎል አስቆጥራለው ሲል ግልፅ ጥፋት ተፈፅሞበት የዕለቱ ዳኛ በዝምታ አልፈውታል። በዚህም ውሳኔ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደስተኛ አልነበሩም።  ከዚህ በኋላ በጣም አስገራሚ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ እድሎችን ሁለቱም ቡድኖች መፍጠር የቻሉ ቢሆንም በተለይ በወልድያው ግብ ጠባቂ ቤሊንጌ ብቃት ምክንያት ጎል ሳይሆኑ ቀርተዋል።

62ኛው ደቂቃ ላይ አበባው ቡታቆ አሻግሮለት አዳነ ግርማ በግንባሩ ገጭቶ ቤሊንጌ ያዳነበት ፣ በ64ኛው ደቂቃ አንዷአለም ንጉሴ ከሳጥን ውጭ መሬት ለመሬት መቶ ሮበርት ያዳነበት 76 እና 77ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ኒኪማ ከርቀት የመታው ኳስ በሀይሉ ብቻውን ነፃ ኳስ አግኝቶ ቤሊንጌ እንደምንም ያዳነበት ኳስ ፈረሰኞቹን ቀዳሚ ማድረግ የሚችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ጨዋታው ከደጋፊዎች የድጋፍ ድባብ ጋር ተጋግሎ ሲቀጥል 83ኛው ደቂቃ ላይ የማሊ ዜግነት ያለው አጥቂው ኬይታ ሲዴ ከግብ ጠባቂው ቤሊንጌ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ለማመን በሚከብድ ሁኔታ የሳተው ኳስ የሚያስቆጭ ነበር። በዚህ ቅፅበት በመልሶ ማጥቃት ወልዲያዎች በፍፁም ገ/ማርያም አማካኝነት የማግባት አጋጣሚ ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ደግሞ አበባው ቡታቆ 88ኛው ደቂቃ ከ30 ሜትር ርቀት የመታውን ቅጣት ምት ቤሊንጌ በአስገራሚ ሁኔታ አድኖበት በጨዋታው ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።

የአሰልጣኞች አስተያየት 

ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ – ወልዲያ 

ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር። ተጫዋቾቼ እንዲያደርጉ የፈለኩትን አድርገው በመውጣታቸው ደስተኛ ነኝ። ኳሱን ይዘን በመጫወት ተጋጣሚን ተጭነን ለመጫወት ነበር አስበን የገባነው። ይህንም ማድረግ ችለናል። በጨዋታው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ደስተኛ ነኝ ። በጉዳት እና ቅጣት የቡድኔን ወሳኝ ተጨዋቾች ባልይዝም ወጣቶቹ ባሳዩት ነገር ሁሉ በጣም ደስተኛ ነኝ።

ፋሲል ተካልኝ – ቅ/ጊዮርጊስ 

ጨዋታው በሁለታችንም በኩል ጥሩ ነበር። ለጨዋታውም ማማር ሁለታችን ክፍት የሆነ ጨዋታ መጫወታችን ይሆናል። እስከዛሬ ካደረግነው እንቅስቃሴ ዛሬ በሁሉም ረገድ የተሻልን ነበር። በተለይ በርካታ የጎል እድል መፍጠር ብንችልም መጠቀም አለመቻላችን አንድ ነጥብ ብቻ ይዘን እንድንወጣ አድርጎናል። ከዚህ በኋላ ተደራራቢ አራት ጨዋታ አለብን። ይህ ለኛ በጣም ከባድ ነው ፤ አወዳዳሪው አካል የጨዋታ መደራረቡን በእኛ ላይ እንዳለ አስቦ ቢያስተካክልልን መልካም ነበር ሆኖም ተወዳደሩ ካለ ከባድ ቢሆንም ውሳኔውን አክብረን እንጫወታለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *