ተሾመ ታደሰ ስለ ጉዳቱ እና በአርባምንጭ ከተማ ላይ ስላለው ቅሬታ ይናገራል

ባለፉት ተከታታይ አመታት በአርባምንጭ ከተማ ወሳኝ ግልጋሎት ሲያበረክቱ ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረው ተሾመ ታደሰ በጉልበቱ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ከሜዳ ከራቀ 7 ወራት አስቆጥሯል፡፡ ሁለገቡ አጥቂ በጉዳት ባሳለፈባቸው ጊዜያት ክለቡ የደሞዝ ክፍያ እንዳልፈፀመለት የገለፀ ሲሆን ከጉዳት ቢያገግምም ቅሬታው ሳይፈታ ወደ ሜዳ የመመለስ ፍላጎት እንደሌለው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጧል፡፡   


ተሾመ ታደሰ ስለ ጉዳቱ ፣ ስለ ቅሬታው እና ቀጣይ እቅዱ ለሶከር ኢትዮጵያ በሚከተለው መልኩ ተናግሯል፡፡

“በ2009 ግንቦት ወር ላይ የጉልበት ህመም አጋጥሞኝ በሆስቲታል ህክምናዬን ተከታተልኩ፡፡ ወደ አዲስ አበባ አምርቼ ኤም.አር.አይ መታየት ስነበረብኝ ያን አድርጌ የህክምና ምርመራ ውጤቱን ይዤ ክለቡ ወጪውን እንዲሸፍን ብጠይቅም ይሄንን ማድረግ አንችልሞ አሉኝ፡፡ እንደገና ወደ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል ሄደህ ታከም ተብዬ በቂ ምርመራ ስላልነበር ወደ ሀዋሳ ሄጄ አላትዮን ሆስፒታል ከታከምኩ በኋላ ያከመኝ ዶክተር ለሶስት ወራት ያክል እረፍት እንደሚያስፈልገኝ ገለፀልኝ፡፡ ነገር ግን ወደ ክለቡ ስሄድ ምላሽ ሊሰጠኝ አልቻለም፡፡ ከዛም በኃላ እስካሁን ባሉት 7 ወራት የደመወዝ ክፍያን ጨምሮ የህክምና ወጪ ሊፈፀምልኝ አልቻለም፡፡ እስከ አሁንም በገባውትን ውል ክለቡ ሊፈፅምልኝ አልቻለም፡፡ ከአንድም ሶስት ጊዜ ለክለቡ በደብዳቤ መሠረት ጥያቄ ባቀርብም ምላሽ ግን ላገኝ አልቻልኩም፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ወደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን መብቴን እጠይቃለሁ ፣ በህግም መሄድ ያለብኝን ርምጃ ሄጄ ለመክሰስ እገደዳለሁ፡፡

“አሁን ላይ በመልካም ጤንነት ላይ እገኛለሁ፡፡ መብቴንም ጠይቄያለሁ ፤ ዛሬ ነገ እየተባልኩ እየተጉላላሁ እገኛለሁ፡፡ ለወጪም እየተዳረኩኝ ነው፡፡ ከሰኔ ጀምሮ ክለቡ ፊቱን አዙሮብኛል፡፡ ውል እያለኝ ለምን ይሄን ሁሉ እንዳደረጉብኝ በግልባጭ ደብዳቤ የሚመለከተውን ሁሉ ጠይቄያለሁ፡፡ እንደ ማንኛውም ተጫዋቾች አሁን ላይ የአርባምንጭ ተጫዋች መሆኔን ነው የማውቀው፡፡ ክለቡ አሁን ላይ ገብቼ እንድሰራ ፈቅዷል፡፡ እኔ ግን ክፍያ እስካልፈፀሙልኝ ድረስ ልሰራ አልገደድም፡፡ ውስጤም ሆነ የመስራት ሞራሌ ተጎድቷል፡፡ ክለቡን በሚገባ ብጠቅምም ክለቡ በምላሹ ምንም ያደረገልኝ ነገር አለመኖሩ እጅግ አሳዝኖኛል፡፡ አሁን ላይ ክለቡ ካልፈለገኝ በርካታ ክለቦች ጥያቄ ስላቀረቡልኝ ክለቡን ለመልቀቅ እገደዳለሁ ”


የተሾመ ታደሰን ቅሬታ ይዘን ለክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ታዲዮስ ጨመሳ ጥያቄን አቅርበን ምላሹን ሰተውናል፡፡

ይሄን ያህል ጊዜን ህመም ላይ መሆኑ እየታወቀ በወቅቱ ክፍያን ያልፈፀማችሁበት ምክንያት ምንድነው ?

እንግዲህ ከኔ በፊት የነበሩት አመራሮች ነበሩ፡፡ ምናልባት እሱ እያለኝ ያለው ከነሱ ጋር በወቅቱ እንዳልተግባባ ነው፡፡ ከቀድሞው ስራ አስኪያጅ እና ከአሰልጣኞቹ ጋርም በአንዳንድ ጉዳዮች እንዳልተስማማ ነበር የገለፀልኝ፡፡ እኔን ለመጉዳት ስላሰቡ እንጂ እንደምጠቅማቸው ያውቃሉ ብሎኛል፡፡

ጉዳዩን በቦርድ ለማየት አስበን ነበር ተሾመ ያነሳቸው ቅሬታዎች በሙሉ እውነት ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት ከኔ ጋርም ቢሮ መጥቶ ነበር፡፡ እኔ አዲስ እንደመሆኔ ቢሮ ውስጥ የሱን ዶክመንቶች ለማየት ሞክሬ ነበር፡፡ የክፍያ ጉዳዮች ላይ ላነሳው ጥያቄ በአግባቡ ክፍያ የምናደርግ ይሆናል፡፡ እስከ አሁን ስለዘገየም ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ ከህክምና ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ላነሳው ጥያቄ ግን የህክምና ወረቀትህን ይዞ እንዲመጣ ጠይቀነው ነበር፡፡ አላመጣም ፤ ነገር ግን ክለቡን ተቀላቅሎ ስራ እንዲጀምር ተገልፆለታል፡፡

በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቦ ምላሽም አልሰጣችሁትም፡፡ ምንም አይነት ክፍያ ሳይፈፀም ወደ ልምምድ ግባ ማለታችሁ ተገቢ ነው?

የህክምና መረጃውን ይዘህልን ና ፤ ነገር ግን የደሞዙን ጉዳይ እንፈታለን ብዬዋለሁ፡፡ የህክምና ማስረጃ በቀጣይ ቀናት ይዘህ ና ብዬዋለው፡፡ ይህንን መረጃ በመያዝ ወደ ቦርዱ እቀርባለሁ፡፡ የህክምናም ሆነ ሌሎች ወጪወችን ለሌሎች ተጫዋቾች እየከፈልን ነው ፤ እሱም ይገባዋል፡፡ ነገር ግን መሟላት የሚገባቸውን መረጃዎች ማሟላት አለበት፡፡ ምናልባት ቴሴራ እንዳይወጣለት የተደረገበት ምክንያት ጉዳት ላይ ስለነበረ እና ማገልገል ላይ ብቁ ስላልሆነ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን ላይ ግን ጤናው ተመልሶ ቡድኑን መጥቀም የሚያስችል አቅም ካለው እንዲመለስ ነው የኛ አላማ፡፡ ቡድኑን የጠቀመ እና ለቡድኑ የደከመ ተጫዋች ነው፡፡ የደሞዙ ክፍያ በአፋጣኝ እንደሚከፈል ለሶከር ኢትዮጵያ ላረጋግጥ እፈልጋለሁ፡፡ ክለቡ ህገ ደንብ አለው፡፡ የቆይታ ጊዜውም ታይቶ ውል ማቋረጥም ከፈለገ ቦርዱን አነጋግረን በአሰራራችን መሠረት ተፈፃሚ እናደርጋለን፡፡

ተሾመ አሁን ላይ የኛ ተጫዋች ነው፡፡ እኛ የአሰራር ክፍተቶች ነበሩብን ፤ ይህንን ክፍተቶች በሚገባ ደፍነን ከእኛ ጋር የሚዘልቅበትን እና ቡድኑን የሚያገለግልበትን መንገድ ማመቻቸት ነው አላማችን፡፡ ስለዚህ በዛ ሁኔታ ተጫዋቹ እንደሚጠቅመንና ከአሁን ቀድም ወደ ቀድሞው ብቃቱ በሚገባ ከተመለሰ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እኛ ጋር እንዲቀጥል ነው ፍላጎታችን፡፡ ከቦርዱ ጋር ተነጋግረን በሚገባ እንፈታዋለን፡፡ አሁን ላይ ወደ ልምምድ እንዲመለስ ነግረነዋል፡፡ አጋጣሚ ሆኖ የክለቡ ቦርድ አባላት ለስራ ከከተማ በመውታቸው የቦርድ አባላት ሲሟሉ ውይይት አድርገን ምላሹን የምናሳውቅ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *